ቀጥታ፡

ኢኮኖሚው ከፈጠረው የዋጋ ጭማሪ በላይ ሰው ሰራሽ ችግሩ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል

ነሀሴ 29 / 2011 (ኢዜአ)  ኢኮኖሚው ከፈጠረው የዋጋ ጭማሪ በላይ ሰው ሰራሽ ችግሩ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት እንደሆነ አንድ ጥናት አመለከተ። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በፍጆታ እቃዎችና አገልግሎቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረትና ህገ-ወጥ ንግድ አስመልክቶ ያካሄደውን የዳሰሳ ጥናት ይፋ አድርጓል። በአገሪቱ ካለፈው ስድስት ወር ጀምሮ በመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በተለይም በምግብ ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለ ነው። በህብረተሰቡ በሚዘወተረው ጤፍ ላይ በኩንታል 400 እስከ 800 ብር፣ከ ስንዴ ከ300 እስከ 600 ብር በኩንታል፣ ሽንኩርት ከ10 እስከ 18 ብር የዋጋ ጭማሪ መታየቱ በጥናቱ ተረጋግጧል። አትክልትና ፍራፍሬም ከተገዙበት በላይ በችርቻሮ በእጥፍ ዋጋ ለህብረተሰቡ እየተሸጡ ነው። ያለምንም ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ጭማሪ ህብረተሰቡን ለምሬት እየዳረገው እንደሆነም ነው ጥናቱ ያመላከተው። የሰብል ምርታማነት በየዓመቱ እድገት እያስመዘገበ ቢሆንም ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ሲነጻጸር በቂ አይደለም። በተጨማሪም በድጎማም ይሁን በሌላ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ተጨማሪ ምርት በውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚፈለገውን ያህል አይደለም። እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ተደማምረው የዋጋ ጭማሪ ቢያስከትሉም እየታያ ያለውን ከፍተኛ የፍጆታ ዕቃ ጭማሪ እንደማያስከትሉ ጥናቱ አረጋግጧል። ካለፈው ስድስት ወር በፊት በአንድ አሀዝ የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ወደ ሁለት አሀዝ ከፍ እያለ መምጣቱንም አሳይቷል።በግብይት ሂደት የደላላ ጣልቃ ገብነት ዋነኛው ችግር መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ በተለይ በመርካቶ፣ መሳለሚያ፣ እህል በረንዳና መገናኛ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዙሪያ ሱሉልታ፣ አሸዋ ሜዳ፣ ጣፎና ሌሎች ክልሎችም ጎልቶ ይታያል ብሏል። በእነዚህ አካባቢዎች የምርት ማከማቸት፣ ፍትሃዊ ባልሆነ የንግድ ውድድር ዋጋ መወሰን፣ ያለ ደረሰኝ መገበያየት፣ የተጭበረበሩ የንግድ ሰነዶችን መጠቀምና በድጎማ የሚወጡ ሸቀጦችን አየር በአየር መሸጥ ተስተውሏል ነው ያለው። አንድ መኪና ፓልም የምግብ ዘይት ደሴ ላይ፤ እንዲሁም አራት መኪና ከነተሳቢው መቀሌ ሊገባ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉን ለአብነት ጠቅሷል። በአዲስ አበባም 1 ሺህ 249 ሊትር የድጎማ ዘይት አየር በአየር ሲዘዋወር መያዙንም እንዲሁ። የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ህግ የማስከበር ድክመትና ለድርጊቱ ተባባሪ መሆን ችግሩን እንደባባሰውም ጥናቱ አክሏል። ችግሩን ለመፍታት ግብረኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ቢገባም ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ አይደለም ያለው ይህ ጥናት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር የተጋነነ ዋጋ የሚጨምሩና ህብረተሰቡን የሚያማርሩ ላይ አስተማሪ ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚያስፈልግ አመላክቷል። የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ህግ የማስከበር ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥብቅ ቁጥጥር እና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው መፍትሄ መሆኑም ጥናቱ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም