በማዕከላዊ ጎንደር ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ቴክኖሎጂ እንዲቀርብ አርሶ አደሮች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ቴክኖሎጂ እንዲቀርብ አርሶ አደሮች ጠየቁ
ጎንደር (ኢዜአ) ነሀሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ባለመሆናችን የምርት ብክነትና የጥራት መጓደል ገጥሞናል ሲሉ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ። አርሶ አደሮቹ የጊዜና የጉልበት ጫናም እየደረሰባቸው በመሆኑ ቴክኖሎጂው እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል። የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ የግል ባላሀብቶች፣ ዩኒየኖችና አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ማሽነሪዎችን በኪራይና በግዢ እንዲያቀርቡ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡ በጣቁሳ ወረዳ የአቸራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታምራት ኃይሉ እንደተናገሩት የተሻሻሉ የግብርና ግብአቶችን በመጠቀም በየዓመቱ ምርታቸውን ማሳደግ ችለዋል፡፡ ይሁንና በሰውና በከብቶች ጉልበት የሚካሄደው የምርት አሰባሰብ ሂደት በአንድ የምርት ዘመን ከሚያገኙት የሰብል ምርት ግማሹ ጥራት እንዳይኖረው ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ "በቀጣይ መንግስት ለምርት መሰብሰቢያና መውቂያ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን የምናገኝበት መንገድ በማመቻቸት እገዛ ሊያደርግልን ይገባል" ብለዋል። "በአውድማ ምርቱን ከገለባ ለመለየት በከብቶች የሚካሄደው አድካሚ የምርት አሰባሰብ ሂደት በትንሹ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ይፈጃል" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ደርብ መላኩ ናቸው፡፡ ከአውድማ ምርቱ እስኪሰበሰብ ድረስ ቤተሰብ ጭምር ቀንም ሆነ ማታ ከሌባ እንደሚጠብቅና ዝናብ ከጣለም የምርት ጥራት እንደሚያጓድልም አመልክተዋል፡፡ "ለሰብል ስብሰባና ምርት ለመውቃት ሥራ ሲባል በየአመቱ ልጆቼን ከትምህርት ቤት ሳስቀር በትምህርታቸው እየተጎዱብኝ ነው" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ቢያዝን አድማሴ ናቸው፡፡ "መንግስት የሰብል ምርታችን እንዲጨምር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በማቅረብ ድጋፍ እንዳደረገው ሁሉ ረጅም ቀናት የሚፈጀውን ኋላቀር የምርት አሰባሰብ ሂደት የሚያስቀር ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ቴክኖሎጂ ሊያመቻችልን ይገባል" ብለዋል፡፡ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዱአለም ሙሉ በበኩላቸው የግል ባለሀብቶች፣ ዩኒየኖችና በማህበር የተደራጁ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በዘርፉ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ማሽኖችን በኪራይ የሚቀርቡበት አስራር ለመተግበር መምሪያው ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱና በሰአት እስከ 10 ኩንታል ምርት መውቃት የሚችሉ በሞተር ኃይል የሚሰሩ የበቆሎ፣ የስንዴና የጤፍ መውቂያ መሳሪያዎች የሚቀርቡበት ሁኔታ እንደሚመቻች ነው የገለጹት። በአርሶ አደሩ በነፍስ ወከፍ በእጅ የሚሰሩ የበቆሎ መፈልፈያና 60 የሚሆኑ የጤፍ መዝሪያዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ አንዷአለም፣ እንደ ኮምባይነር ያሉ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ መሳሪያዎች በዞኑ እንደሌሉ ገልጸዋል፡፡ የሰውና የእንስሳትን ጉልበት በመጠቀም በሚካሄደው የምርት አሰባሰብ ሂደት ባለፈው ዓመት ብቻ ከ237ሺህ ኩንታል በላይ የምርት ብክነት እንደደረሰ በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ የጸሐይ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አቤ ዩኒየኑ በቀጣዩ ዓመት የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ ለምርት መሰብሰቢያና መውቂያ የሚያገለግሉ ኮምባይነሮችን ለአርሶ አደሩ በኪራይ ለማቅረብ ማቀዱን ተናግረዋል፡፡ ዩኒየኑ 120ሺህ ለሚሆኑ አባል አርሶ አደሮቹ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ጸረ አረምና ጸረ-ተባይ ኬሚካል በየዓመቱ እያቀረበ ነው፡፡ "የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት የሚቀንሱና የምርት ጥራትና ብክነትን የሚያስወግዱ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን ዪኒየኑ የፋይናንስ አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ገዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅም ይሰራል" ብለዋል፡፡ በዞኑ ኑሯቸውን በግብርና ሥራ ላይ የመሰረቱና አነስተኛ የእርሻ ይዞታ ያላቸው ከ300ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር በ2011/12 ምርት ዘመን ታርሶ በዘር ከተሸፈነው 500ሺህ ሄክታር መሬት 14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡