የሰላምና የጸጥታ ችግር የሆቴልና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ሊታሰብበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሰላምና የጸጥታ ችግር የሆቴልና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ሊታሰብበት ይገባል
ነሐሴ 28/2011 በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የሰላምና የጸጥታ ችግር የሆቴልና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ሊታሰብበት ይገባል ተባለ። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የሆቴል ፌዴሬሽንና ማህበራት ያዘጋጁት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ጉባኤ ተካሂዷል። በጉባኤው ተሳታፊ የነበሩ በዘርፉ የተሰማሩ ባለኃብቶች እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በአገሪቷ የታየው የጸጥታ መደፍረስ ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በዚህ ዘርፍ ከተሰማሩት ባለሃብቶች መካከል አንዱ የሆነው ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የሰላም ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ አስገንዝቧል። ''ጎብኚዎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ከፍተኛ ሁከትና ብጥብጥ ሳይሆን ትንሽ የሚመስሉ መንገድ ላይ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች ናቸው'' ብሏል። በመሆኑም ዘርፉ ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም ይቻል ዘንድ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጿል። የኢትዮጵያ ሆቴል አሰሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት እንደሚሉት፤ ሌሎች የዘርፉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው የሰላም ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ''እስካሁንም ባለው ሁኔታ የሰላምና ጸጥታ መደፍረስ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል'' ብለዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የሰላምና የጸጥታ መደፍረስ ባጋጠመባቸው ቦታዎች ቀዳሚ ሰለባ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግስት የሰላም መደፍረስ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያስከትል እየሰራ ሲሆን በቀጣይም አሁን የተጀመሩትን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አሁን በክልሉ የተሻለ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁመዋል። በቀጣዩ ዓመት መንግስት ይህንኑ ሰላምና ጸጥታን የማስከበር ስራ በተሻለ መልኩ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችም የተመለሱ ሲሆን ለኢንቨስትመንት ስጋት የሚሆን ነገር ባለመኖሩ ባለሃብቶች በክልሉ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል። የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዲሁ ከሁለት ወራት ወዲህ በክልሉ የተሻለ የሰላም ሁኔታ መኖሩን ተናግሯል። ወደፊትም ክልሉ ለሚያከናውነው ሰላምንና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራዎች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉት ጠይቀዋል። ሌሎች የክልል ተወካዮችም በጸጥታ ጉዳይ እንደማይደራደሩ ገልጸው፤ ባለሃብቶች በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል። በውይይቱ ላይ ለተለያዩ አካላት የምስጋናና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።