ከሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሻሻል የዘርፉ ማነቆዎች ሊፈቱ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ከሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሻሻል የዘርፉ ማነቆዎች ሊፈቱ ይገባል ተባለ
ነሐሴ 28/2011 በኢትዮጵያ ከሆቴልና ቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ማሻሻል እንዲቻል ከዘርፉ ጋር በተያያዘ ያሉትን ማነቆዎች መፍታት እንደሚገባ ባለኃብቶች አሳሰቡ። መንግስት በበኩሉ ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ጉባኤ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሄዷል። በጉባኤው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የክልል መንግስታት ርእሰ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለኃብቶች ተገኝተዋል። በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም ኃብት አላት ፤ ሆኖም የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ከዘርፉ መጠቀም አልቻለም ሲሉ የዘርፉ አንቀሳቃሾች ገልፀዋል። የኢትዮጵያን አጠቃላይ የሆቴልና ቱሪዝም ልማት የተመለከተ ጥናት ያቀረቡት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው እንደሚሉት፤ አገሪቷ ከበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦቿ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ችለላለች። ከነዚህ መካከል ምግብና አመጋገብ፣ አስገራሚ የተፈጥሮ ሃብቶች፣ ባህላዊና ኃይማኖዊ ክንውኖች፣ የስፖርት፣ የፍል ውኃና የቡና ቱሪዝም ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል። ምንም እንኳን ዘርፉ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ዜጋ መተዳደሪያና ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚያስገኝ ቢሆንም አሁንም ከፍተኛ ችግር አለበት ባይ ናቸው ጥናት አቅራቢው። ''የመሰረተ ልማት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም ምቹ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ሁኔታ አለመኖር ዘርፉ ከተጋረጡበት ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው'' ብለዋል። የአዲስ አበባ የሆቴሎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ብስራት ያለውን የሰው ኃይል ወደሰው ኃብት ለመቀየር የማሰልጠኛ አካዳሚ አለመኖር ሌላው ችግር እንደሆነ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም እስካሁን በአገሪቱ የተገነቡት ባለኮከብ ሆቴሎች የገበያ ተደራሽ እንዲሆኑ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በመዲናዋ እንዲካሄዱ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል። ፕሬዚዳንቱ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዘርፉን ይበልጥ ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅሰዋል። በጉባኤው ላይ ከቀረጥ ነጻ እቃዎችንና ተሽከርካሪዎችን የማስገባትና ከታክስ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉ ተነስቷል። ህገ ወጥ የአገር ውስጥና የውጪ አገር አስጎብኚዎች በስፋት እየተንቃሳቀሱ መሆኑ ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሆነም ተገልጿል። በጉባኤው ላይ የተገኙት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በውይይቱ ላይ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከታክስ እፎይታ ጋር በተያያዘ የታክስ ክፍያው እንደየ ሁኔታው እንዲራዘም መደረጉን ተናግረዋል። ''በተለያዩ ምክንያቶች ለኪሳራና ለጉዳት የተዳረጉ ኢንቨስትመንቶችን የተመለከቱ መረጃዎች እየተጣሩ ፈጣን ምላሽ እየተሰጠ ነው'' ብለዋል። ''አንዳንድ አስጎብኚዎችና ሆቴሎች ከቀረጥ ነጻ ማበረታቻውን ያለአግባብ ተጠቅመውበታል'' ያሉት ሚኒስትሯ፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ከቀረጥ ነጻ የገቡ 500 ተሽከርካሪዎች ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ሲሸጡ ሲሉ መያዛቸውን ገልፀዋል። የመሰረተ ልማት ችግርን በተመለከተ በተለይ ደግሞ የመንገድና የአየር ትራንስፖርት በተሻለ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ መንግስት እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል። የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንደሚሉት፤ መንግስት የኮንትራክተሮችን አቅም በማሳደግ የመንገድ መሰረተ ልማትን የቱሪስት መዳረሻ ድረስ ለማዝለቅ ይሰራል። በተያዘው በጀት ዓመት ካሉት 23 አየር ማረፊያዎች አምስት አዳዲስ ለመገንባት መታቀዱንና ክልሎች የአውሮፕላን ማረፊያ ማኮብኮቢያዎችን እንዲሰሩ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ''መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል'' ብለዋል። እስካሁንም በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ቱሪዝም አንዱ እንዲሆን ተወስኖ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የዘርፉን ችግሮች ለመፍታትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።