ላለፉት 11 ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አላገኘንም - የደብረ ማርቆስ ከተማ የልማት ተነሽዎች - ኢዜአ አማርኛ
ላለፉት 11 ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አላገኘንም - የደብረ ማርቆስ ከተማ የልማት ተነሽዎች
ደብረ ማርቆስ ሰኔ 7/2010 በደብረ ማርቆስ ከተማ ላለፉት 11 ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን የልማት ተነሽዎች ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡ ቅሬታቸውን ለኢዜአ የገለፁ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት በደብረማርቆስ ከተማ ዙሪያ የነበራቸው የእርሻ መሬትና የመኖሪያ ቤታቸው ለኢንቨስትመንት አገልግሎት በመፈለጉ ይዞታቸውን አስረክበው ምትክ ቦታ ከተሰጣቸው 11 ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ከልማት ተነሽዎቹ መካከል የቀበሌ 05 ነዋሪ አቶ ሙሉየ ተገኘ እንደተናገሩት ይዞታቸው ለኢንቨስትመንት እንዲውል ከ11 ዓመት በፊት አስረክበው በምትኩ በከተማው ቀበሌ 05 የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቢሰጣቸውም እስካሁን የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ በወቅቱ መንግስት ከሰጣቸው የካሳ ክፍያ ለመሰረተ ልማት ማሟያ ተብሎ ከእያንዳንዱ ተነሽ አንድ ሺህ ብር ተቀንሶ እንደተሰጣቸው አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የውሃ መስመር ከማስገባት በሰተቀር የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን በየጊዜው ለከተማ አስተዳደሩ መዘጋጃ ቤት ቢጠይቁም አመራሩ በመገፋፋት ጉዳያቸውን ትኩረት አለመሰጠቱን ገልጸዋል። አቶ ልየው ወርቁ የተባሉ ቅሬታ አቅራቢ በበኩላቸው ለነበራቸው ይዞታ ከ50 ሺህ ብር ያልበለጠ ግምት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ ከነበሩበት የገጠር አካባቢ ወደ ከተማ በመግባታቸው ደስታ የፈጠረባቸው ቢሆንም ከመጡ በኋላ ከገጠሩ ያልተናነሰ ኑሮ እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተሰጣቸው የካሳ ክፍያም ለመተዳደሪያ የሚሆኑ ከ10 በላይ ክፍሎች ቢሰሩም መብራት ባለመኖሩ የሚከራይ አጥተው ለኪሳራ መዳረጋቸውን ገልጸዋል። ወይዘሮ አይናዲስ መኩሪያው በበኩላቸው መብራት ባለማግኘታቸው ለመብራት የሚሆን ነዳጅና የማገዶ እንጨት በመግዛት ጠላ ሽጠው ከሚያገኙት ገቢ በላይ ወጪ እየጠየቃቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው ክፍል ችግራቸውን ተረድቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ የከተማ አስተዳሩ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ዝግያለ ካሳ በበኩላቸው ግለሰቦቹ ያነሱት ችግር መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ''ሆኖም ግን በቦታው ከተመደብሁ አጭር ጊዜ በመሆኑ ባለፉት ጊዜያት ለምንና በምን ሁኔታ አገልግሎቱን ማግኘት እንዳልቻሉ ዝርዝር መረጃ የለኝም'' ብለዋል፡፡ ''አሁን ግለሰቦቹ እያቀረቡት ያለው ጥያቄም 'ከቦታው ስንነሳ ከተሰጠን የካሳ ክፍያ ለመብራትም የተቆረጠ በመሆኑ መንግስት ሙሉ በሙሉ ግምቱን በመሸፈን ሊያስገባልን ይገባል' የሚል ስለሆነ መረጃውን ማግኘትና ትክክለኛውን ማረጋገጥ ይገባል'' ሲሉ ገልፀዋል። ''ይሁን እንጀ ትክክለኛውን መረጃ በቦታው የነበሩ ግለሰቦችን በማነጋገርም ሆነ ሰነዶችን በመመርመር እስኪታወቅ ድረስ መጎዳት ስለሌለባቸው መፍትሔ ለመስጠት ጥረት ይደረጋል'' ብለዋል። ስለሆነም ከአራት ወራት በፊት የመብራት ሀይል ባለሙያዎችን ከክልል በማስመጣት የትራንስፎርመር ግምት አውጥተው የሄዱ ሲሆን በሚቀጥለው የበጀት ዓመት መንግስት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል። በልማት የተነሱት 45 አባወራዎችና እማወራዎች ከ200 በላይ የቤተሰብ አባለት እንዳሏቸው ታውቋል።