ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የትራንዚት ተኮር ልማት ፕሮጀክት የፋይናንስ ስትራቴጂ ዝግጅት ተጠናቋል

ነሐሴ 28/2011 የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የትራንዚት ተኮር ልማት ፕሮጀክት የፋይናንስ ስትራቴጂ የማዘጋጀት ሂደት መጠናቀቁ ተገለጸ። በፋይናንስ ስትራቴጂው ዙሪያ የባለድርሻ አካላት አውደ ጥናት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል። የትራንዚት ተኮር ልማት ፕሮጀክት ከቀላል ባቡር መሠረተ ልማት ከ800 ሜትር እስከ አንድ ሺህ ሜትር በሚገኝ ራዲየስ ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን በማልማት የህዝቡን ኑሮ በማዘመንና ቀላል በማድረግ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል ማዕቀፍ ነው። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ከመንግስትና አጋር አካላት በተገኘ የ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የአዋጪነት ጥናት አድርጎ 19 ቦታዎች ቢለዩም ፕሮጀክቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ለማስቻል ወደ 13 ዝቅ እንዲል ተደርጓል። በመጨረሻም ለገሃር፣ ቅድስት ልደታ፣ አውቶቡስ ተራና ዳግማዊ ምንሊክ አደባባይ የባቡር ጣቢያዎች  ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ለፕሮጀክቱ የሚሆን ገንዘብ የማፈላለግ ስራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ከደቡብ ኮሪያ መንግስት በተገኘ የ3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ ኮሪያ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማዕከልና የታዳሽ ሃይል ኩባንያ ኢንቨሎፕስ የፕሮጀክቱን ፋይናንስ ስትራቴጂውን ማዘጋጀታቸው ታውቋል። የፋይናንስ ስትራቴጂውን አስመልክቶም በዛሬው ዕለት ገለጻ ሲያደርጉ እንዳመለከቱት፤ የፋይናንስ ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ የምክክር መድረኮች መዘጋጀታቸውንና ለፕሮጀክቱ ስራ ተሳታፊ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላትን የመለየት ስራ ተከናውኗል። የደቡብ ኮሪያው የታዳሽ ሃይል ኩባንያ ኢንቨሎፕስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስ ሱን ኪም ፕሮጀክቱ ከአየር ንብረት ጋር የተስማማ እንዲሆን የሚያስችል ንድፍ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ያልነበረ ለትራንዚት ተኮር ልማት የሚሆን የተቀናጀ የፋይናንስ መዋቅር መዘጋጀቱንና የስራ ሂደቱን የሚገልጽ ሰነድ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። ፕሮጀክቱ ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገባና የአውቶቡስ የአስተዳደርና መረጃ ስርአትን በሌሎች የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመዘርጋት 68 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል። የደቡብ ኮሪያ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማዕከል የአየር ንብረት ለውጥ ቴክኖሎጂ ትብብር የስራ ክፍል ሃላፊ ሚስ ሱ ክዩንግ ሊ በበኩላቸው ''የተቀመጠውን የገንዘብ መጠን ለማግኘት ከአጋር አካላት ገንዘብ የማፈላለግ ስራ በኮሪያ መንግስት በኩል ይከናወናል'' ብለዋል። ማዕከሉ በተለይም ከደቡብ ኮሪያ የልማት እርዳታ ፕሮግራም (ኦዳ) እና ከደቡብ ኮሪያ መንግስት ገንዘብ በሚገኝበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚያደርግም አመልክተዋል። የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን (ዩኤንኤፍሲሲሲ) ለማስፈጸም የተቋቋመ መቀመጫውን በዴንማርክ ያደረገው የአየር ንብረት ለውጥ ቴክኖሎጂ ማዕከልና ትስስር ተቋም ሌላኛው የፋይናንስ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ምድር ኮርፖሬሽን የንግድ ስራዎች ማበልጸጊያ መምሪያ ሃላፊ አቶ ሸዋንግዛው ክፍሌ ''ለፕሮጀክቱ ትግባራዊነት ከከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው'' ብለዋል። በ13 ሚሊዮን ብር ወጪ የመሬት ይዞታና ቦታ ካርታ መዘጋጀቱንና የተዘጋጀው ካርታ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸዋል። በባቡር መተላለፊያ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ብዛት በመረጃ መጠናከሩን ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ የቴክኒክና የስትሪንግ ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል። የትራዚት ልማት ፕሮጀክቱ የሚቆይበት ጊዜ ስፋትና በፕሮጀክቱ ውስጥ የሚከናወኑ ዝርዝር ስራዎች ለፕሮጀክቱ እንደሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሚወሰን እንደሚሆንም አቶ ሸዋንግዛው አስረድተዋል። የትራንዚት ተኮር ልማት(TOD) የከተማ ልማትን በማበረታታት፣ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን በማሳደግ፣ አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ ፍትሃዊ የሃብት አጠቃቀም በማስፈን፣ ወጪን በመቀነስና የኢንቨስትመንት ወጪን በመተካት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት በአውደ ጥናቱ ወቅት ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም