የዋሺንግተን ከንቲባ በአዲስ አበባ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የዋሺንግተን ከንቲባ በአዲስ አበባ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑ ተገለጸ
ነሐሴ 28/2011 የዋሺንግተን ከንቲባ ሙሪል ቦውዘር አዲስ አበባን በቅርቡ እንደሚጎበኙ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ። አምባሳደር ፍጹም እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል። በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የአሜሪካ መንግሥት ለአፍሪካ በከፈተው "አፍሪካን ማበልጸግ" አዲስ ፖሊሲ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል። አሜሪካ በምጣኔ ኃብት ዘርፍ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችው የማሻሻያ ርምጃ በአፍሪካን ማበልጸግ ፖሊሲ ለመጠቀም ምቹ መደላድል መፍጠሩን ጠቁመዋል። በግንቦት ወር ለሁለት ቀን በአሜሪካና በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ልውውጥ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ መደረጉን አስታውሰዋል። በዚህም 400 ኩባንያዎች መሳተፋቸውን ገልጸው፤ የመንግሥትና የግል ባለኃብቱ ጥምረትን ጨምሮ ሌሎችም ፖሊሲዎች ይፋ በመደረጋቸው ለባለኃብቶቹ መነቃቃት መፍጠሩን ጠቁመዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአሜሪካ ጉብኝት ከዳያስፖራ ማኅበረሰቡ ጋር በመቀራረብ ትልቅ እመርታ ማምጣቱን አምባሳደር ፍጹም ተናግረዋል። በርካታ ሰዎች በሚያራምዷቸው የፖለቲካ አስተሳሰቦች 'ወደ አገሬ አልሄድም' ብለው ተስፋ ቆርጠው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ መቻላቸውን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ኤምባሲና አምባሳደር ጋር ተቀራርቦ መስራት መጀመሩን ጠቁመዋል። በአትላንታ የተካሄደው ዓመታዊ የእግር ኳስ ጨዋታ መርኃ ግብርን አብሮ መስራት መጀመሩን የሚያሳይ ተምሳሌት መሆኑን አንስተዋል። ''በ14 ከተሞች በመዘዋወር የተደረጉት ስብሰባዎች ከዳያስፖራው ጋር ለተገኘው መቀራረብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አሏቸው'' ነው ያሉት። በሌላ በኩል ከረድኤት ድርጅቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተጀመሩትን ትብብሮች ማጠናከርና አዲስም ለማስጀመር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አስረድተዋል። በዚህም እነዚህ ድርጅቶች የሆስፒታሎች የህክምና መርጃ ማሣሪያዎችን በአካልም ተገኝተው ሙያዊ ድጋፍ ማድረጋቸውንና ሥልጠና መስጠታቸውን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩና የተማሪዎችና የመምህራን ልውውጥ መደረጉን ጠቅሰዋል። በእህትማማችነት ከተሞችን ለማገናኘት በተደረገው ጥረት ዋሺንግተን ከተማን ከአዲስ አበባ ጋር ለማቀራረብ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል። በዚህም ረገድ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በዋሺንግተን ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ''በቅርቡም የዋሺንግተን ከንቲባ ሙሪል ቦውዘር አዲስ አበባ ይመጣሉ'' ብለዋል። ጎን ለጎንም በኮሎራዶ ውስጥ ያሉ ዴንቨር ከተማን ለባህርዳር እንዲሁም አሮራን ከአዳማ ጋር ትብብር እንዲፈጥሩ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ከመቼው ጊዜ በላይ መልካም የግንኙነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት።