የሚኒሶታው ቆንስላ ጽህፈት ቤት አገልግሎቱን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማድረስ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሚኒሶታው ቆንስላ ጽህፈት ቤት አገልግሎቱን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማድረስ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 28/2011 በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ከአማርኛና እንግሊዝኛ በተጨማሪ በኦሮምኛና በሶማልኛ ቋንቋዎች አገልግሎት ለመሥጠት እየሰራ መሆኑን ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ ገለጹ። በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የቆንስል ጄኔራል አምባሳደሩ እውነቱ ብላታ እንደተናገሩት፤ ቆንስላው ዜጎችን ከአገራቸው ጋር ለማቀራረብ የተከፈተ ነው። ጎን ለጎንም ዜጎች ለአገራቸው የተለያዩ እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎችን እንዲያስተዋውቁ እንዲሁም አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማስቻልም። ከተከፈተም በኋላ በተለይም በሚኒሶታና አካባቢዋ በሚገኙ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበረሰብ መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማሻሻል ትልቅ እመርታ ተገኝቷል ብለዋል። በግዛቷ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አብሮነትን በተመለከተም ጫፍ የረገጠና መራራቅ የተላበሰ ይህም ለበርካታ ዓመታት የቆየ እንደነበር አስታውሰዋል። በተለይም አብዛኞቹ የፖለቲካ ስደተኛ ስለሆኑ ነገሮች ፖለቲካዊ ገጽታ እንዲላበሱና በዜጎች መካከል መቃቃር እንዲኖር ማድረጉን ተናግረዋል። አሁን ላይ ይህ አይነቱ ችግር መቃለሉን ገልጸው ለዚህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የአሜሪካ ጉብኝት ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት። እንዲያም ሆኖ በአካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ ጉዳይ አብሮ ለመሥራት አሁንም በርካታ ሥራዎችን ይጠይቃል ብለዋል። ይህንንም ለማድረግ በዲያስፖራ ማኅበረሰቡ በተቋቋሙ ማኅበራት አማካይነት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በሚኒሶታ ብቻ ሳይሆን ቆንጽላው በሚሰራባቸው 12 ግዛቶችም ተመሳሳይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ የአንድ ማኅበረሰብ መገለጫ ሆኗል የሚሉ ወቀሳዎች ይቀርባሉ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄም "እኛ እንደዚህ አይነት ቅሬታ አልሰማንም" በማለት አስተባብለዋል። ጽህፈት ቤቱ እንደማንኛውም ኤምባሲና ቆንስላ ተመሳሳይ አገልግሎት አየሰጠ መሆኑን ገልጸው ይህም ለሁሉም በእኩል እየተዳረሰ መሆኑን አስረድተዋል። ያም ሆኖ በሚኒሶታ በሚገኘው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ስብጥር በአመዛኙ የኦሮሞና የሶማሌ ብሔር ተወላጅ ዜጎች እንደሚገኙ ገልጸዋል። እነዚህ ዜጎች ቆንስላው በመደበኛነት በአማርኛና በእንግሊዝኛ የሚሰጠውን አገልግሎት በኦሮምኛና በሶማልኛም እንዲያደርግ መጠየቃቸውንና ይህንኑ ለመተግበር እየሰራ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል።