ኢትዮጵያን ከቀርከሃ ሃብት ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ከቀርከሃ ሃብት ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ
ነሐሴ 28/2011 ኢትዮጵያ የቀርከሃ ሃብቷን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችላት ብሔራዊ የቀርከሃ ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ። ቀርከሃብ ወደ አረንጓዴ አኮኖሚ ዕድገት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማስገባት የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እና ”ደች-ሲኖ-የምስራቅ አፍሪካ ቀርከሃና ሸንበቆ የልማት ፕሮጀክት” ምክክር እያደረጉ ነው። ምክክሩ በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን የኢትዮጵያ የቀርከሃ ሃብት ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን ዘርፉ የደረሰበትን ዓለምአቀፋዊ ተሞክሮ ያመላከተ ነው። ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 47 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የቀርከሃ ሃብት እንዳላት ይገለጻል። የ750 ሺህ ዜጎችም መተዳደሪያ ነው። ይህን ሃብቷን በማሳደግ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2030 ከአፍሪካ ቀዳሚ አቅራቢ ለመሆን ነው የ10 ዓመት ስትራቴጂ ያዘጋጀችው። ስትራቴጂው ከመስከረም 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሲሆን ከዚህ በፊት በዘርፉ የነበረን የክህሎት፣ የማምረቻ ቴክኖሎጂ እና ዝቅተኛ ተጠቃሚነት በመቀየር ከውጭ የሚገባውን በአገር ውስጥ የሚተካ ጭምር ነው ተብሏል። ቀደም ሲል አገሪቱ ከዘርፉ መጠቀም የሚያስችላት ስትራቴጂ ባለመኖሩ 10 ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ወጪ የቀርከሃ ምርቶችን ከውጭ ማስገባቷን ባለፈው ዓመት የተጠና ጥናት አሳይቷል። የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የቀርከሃ ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አሸብር ወንድሙ፤ ቀርከሃ ለአካባቢ ስነ-ምህዳር ተስማሚነትና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስኬት ሲባል ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች 200 ሺህ ሄክታር በቀርከሃ ለመሸፈን መታቀዱን ነግረውናል። ይህም አገሪቱ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸው ይፋ የሆነውን የ10 ዓመታት ስትራቴጂ ስኬታማ ያደርገዋል ብለዋል። እንዲሁም ከፌዴራል እስከ ወረዳ የራሱን አደረጃጀት በመፍጠር የሙያ ተቋማትና የግሉን ዘርፍ ያሳታፈ የስልጠናና ፈጠራ ማዕከላት እንደሚቋቋሙ፤ ባህላዊ አምራቾችን በማደራጀትም ዘርፉን እንዲያዘምኑ እንደሚሰራ አቶ አሸብር ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ኬንያና ኡጋንዳን አስከትላ በቀርከሃ ሽፋኗ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት ተርታ ስትሰለፍ፤ በተጠቃሚነት ግን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። መድረኩ አትዮጵያን ጨምሮ ለኬንያና ኡጋንዳ የቀርከሃ አቅምን ለማሳደግና ተጠቃሚነትን ለማሻሻል በሚሰራው 'ደች-ሲኖ-የምስራቅ አፍሪካ ቀርከሃና ሸንበቆ የልማት ፕሮጀክት’ የተዘጋጀ ነው። ከአትዮጵያ፣ ከኬንያና ኡጋንዳ እንዲሁም ፕሮጀክቱን ከሚደግፉት ኔዘርላንድስ እና ቻይና የተውጣጡ ባለሙያዎች የመድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቻይና እና ኔዘርላንድስ በቀርከሃ ተጠቃሚነት ቀዳሚ መሆናቸው ይታወቃል።