ለድርጅቱ ማቋቋሚያ የሚያስፈልገው ከ797 ሚሊዮን ብር በላይ አልተሰጠውም - ኢኢግልድ - ኢዜአ አማርኛ
ለድርጅቱ ማቋቋሚያ የሚያስፈልገው ከ797 ሚሊዮን ብር በላይ አልተሰጠውም - ኢኢግልድ

ነሀሴ 28 ቀን 2011 የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት ገንዘብ ሚኒስቴር ለድርጅቱ ማቋቋሚያ መስጠት የነበረበትን ከ797 ሚለዮን ብር በላይ አልሰጠኝም አለ። ድርጅቱ የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸሙንና የ2012 ዕቅዱን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ እንደገለጹት ድርጅቱ በ2011 በጀት ዓመት በርካታ የኢንዱስትሪ ግብዓት ተግባራትን ቢከውንም በካፒታል በኩል የገጠሙት ተግዳሮቶች አልተፈቱም። ድርጅቱ በ2006 ዓ.ም ሲቋቋም ከገንዘብ ሚኒስቴር በጥሬ ገንዘብ ሊሰጠው የሚገባው ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ እስካሁን እንዳልተሰጠው አስታውቀዋል። በተጨማሪም ከ2003-2004 ዓ.ም ከራሱ በጀት 596 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በማውጣት ዘይት እንዲያቀርብ የተደረገ ቢሆንም ገንዘቡ ከሚኒስቴሩ ተመላሽ አልተደረገለትም። ዋና ስራ አስፈጻሚው ጉዳዩን ሲያብራሩ "የዘይቱ ሽያጭ ገቢ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል 'የዘይት አካውንት' ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን እስካሁን ለድርጅቱ አልተመለሰም" ብለዋል። ለጉዳዩ መፍትሄ ለመሻት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት የተካሄደ ቢሆንም 'ይመለሳልም አይመለስምም' የሚል ምላሽ እንዳልተሰጠበት አንስተዋል። 'ገንዘቡ መመለስ አለበት' የሚል አቋም ይዘን እየሰራን ነው ያሉት አቶ ወንዳለ የማይመለስ ከሆነ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በሚፈለገው ልክ ግብዓት ለማቅረብ 'እንቸገራለን' ነው ያሉት። ይህ ደግሞ ድርጅቱ ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ እየሰራ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚገታው ነው ያስታወቁት። ድርጅቱ ባለበት የካፒታል እጥረት የተነሳ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያቀርባቸውን የፍጆታ እቃዎች በሚፈለገው ልክ መከወን እንዳልቻለም አክለዋል። በሌላ በኩል ድርጅቱ የካፒታል እጥረት ቢያገጥመውም ያለውን አቅም በመጠቀም በበጀት ዓመቱ ለማከናወን በዕቅድ ከያዛቸው ተግባራት ከ90 በመቶ በላይ መፈጸሙን ገልጸዋል። ለስኬቱ የድርጅቱ ሠራተኞች ቀዳሚ በመሆናቸው የላቀ አፈጻጸም ላሳዩት የሁለት እርከን የደረጃ ዕድገትና የሁለት ወር ደሞዝ ጉርሻ እንደተሰጣቸው ጠቅሰዋል። ድርጅቱ በ2011 በጀት ዓመት ከ166 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ለጨርቃጨርቅ፣ ለቆዳ፣ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎችና ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅርቧል። ለተለያዩ የምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እና በክልሎች ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችም 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ከ586 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር አሰራጭቷል። በ2012 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ማቀዱም ተገልጿል።