ነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ተሰጠ
ነሀሴ 28 ቀን 2011 በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል በተደረገላቸው ነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸውን የአገልግሎቱ ተጠቃዎች ገለፁ፡፡ ሪፈራል ሆስፒታሉ በበኩሉ ለአንድ ሳምንት በሰጠው ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ከ800 በላይ ህሙማን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጿል፡፡ ከሕክምናው ተጠቃሚዎች መካከል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሀቢባ መሃመድ እንደገለጹት የሁለት ዓይኖቻቸውን ብርሃን አጥተው በቤት ውስጥ መዋል ከጀመሩ ዘጠኝ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጤና ተቋማት ከ4 ሺህ ብር በላይ አዉጥተዉ ህክምና ቢያደርጉም ብርሃናቸዉ ሊመለስ እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ አሁን ግን በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል በተደረገላቸው ነጻ የዓይን ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የዓይን ብርሃናቸው በመመለሱ መደሰታቸዉን ገልጸዋል፡፡ እድናለሁ የሚል ተስፋ እንዳልነበራቸዉ የሚናገሩት ወይዘሮ ሀቢባ ብርሃናቸዉ ተመልሶ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ሌላው በወረባቦ ወረዳ የ027 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቃሲም ከድር በበኩላቸው አይናቸዉ በእርጅና ምክንያት ማየት ተስኖት እይታ ካቆመ ከ11 ዓመት በላይ ማስቆጠሩን ገልጸዋል፡፡ በግላቸው ለመታከምም ከአቅማቸው በላይ ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቃቸው ብርሃን አጥተው ለመቆየት መገደዳቸዉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የግብርና ስራቸውን ለማከናወንና እንደልባቸው ወጥተው ለመግባት ተስኗቸው ለጥገኝነት ተዳርገው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ አሁን በተደረገላቸዉ ህክምና የአይናቸዉ ብርሃን ተመልሶ ማየት በመጀመራቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ እድሉን አጥተዉ በየቤታቸው የሚሰቃዩ ሌሎች ወገኖች በመኖራቸው መንግስት ህክምናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል፡፡ የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት ሆስፒታሉ ከነሃሴ 17 እስከ 24 በሰጠዉ ነጻ የአይነ ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና 800 ህሙማን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ በተደረገላቸዉ ህክምና በሞራ ተሸፍኖ የነበረዉ የአይን ብሌናቸው ተስተካክሎ ማየት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ሰይድ ገለጻ አብዛኛዉ ታካሚዎች ከደቡብ ወሎና ከኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳር ዞን የመጡ ሲሆኑ በዕድሜ መግፋት፣በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያ ማየት የተሳናቸዉ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ የዓይን ሞራ ሕክምና የሚደረግላቸው ሕሙማን ከሕክምናው በተጨማሪ በሆስፒታሉ በሚቆዩበት ጊዜ የምግብና የትራንስፖርት ወጪ እንደተሸፈነላቸውም ገልፀዋል፡፡ የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸዉ ነጻ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ከ10 ሺህ በላይ ህሙማን የዓይን ብርሃናቸው እንዲመለስ ማድረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡