የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን እየተረቀቁ ያሉት ሕጎች አብዛኞቹ መጠናቀቃቸው ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን እየተረቀቁ ያሉት ሕጎች አብዛኞቹ መጠናቀቃቸው ተጠቆመ
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 28/2011 በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመንና የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አያያዙን ማጠናከር ይቻል ዘንድ ሲካሄድ የቆየው የህግ ማሻሻልና ማርቀቅ ተግባር በአብዛኛው እየተጠናቀቀ መሆኑን የሕግና ፍትሕ አማካሪ ምክር ቤት አስታወቀ። የተሻሻሉትና አዲስ የተረቀቁት ሕጎች ለሚኒስተሮች ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላካቸውንም የጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ጽህፈት ቤት ገልጿል። የፀረ-ሽብር ህጉንና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅን ጨምሮ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲ ትግበራ እንቅፋት ናቸው ተብለው ወቀሳ የሚቀርብባቸው የተለያዩ የህግ ማእቀፎች አሉ። መንግሥትም ይህንን ሁኔታ መለወጥ እንዲቻል የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመንና የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አያያዙን ማሻሻል ይቻል ዘንድ በበጎ ፈቃድ የሚሠሩ 13 አባላት ያሉት የሕግ ባለሙያዎችን ያቀፈ አማካሪ ምክር ቤት ያቋቋመው ከአንድ ዓመት በፊት ነው። በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ ላለፈው አንድ ዓመት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን የአማካሪ ምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የሰብአዊ መብት ጠበቃው ዶክተር አባድር መሐመድ በተለይ ለኢዜአ ተናግረዋል። ዶክተር አባድር እንደሚናገሩት በሕግ ማርቀቅ ሂደቱ ከ153 በላይ የሕግ ሙህራን ተሳትፈዋል። ከኅብረተሰቡ ፣ ከመንግስት አስፈጻሚዎች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግብዓት ለማሰባሰብ የሚረዱ ሰፊና ጥልቅ የምክክር መድረኮችም ተካሂደዋል። አማካሪ ምክር ቤቱ ካካሄደው ጥናትና የውይይት መድረክ በመነሳትም የፍትሕ ሥርዓቱን የሚያዘምኑና የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ አያያዙን ለማሻሻል የሚያግዙ 12 ሕጎች እና አዋጆች መዘጋጀታቸውን ዶ/ር አባድር አክለው ጠቁመዋል። ከተሻሻሉትና ከተረቀቁት ሕጎች መካከል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ፣ የኮምፒውተር ወንጀልን ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ፣ የመረጃ ነጻነትን ለመደገፍ የወጣ አዋጅና የመገናኛ ብዙሃል አዋጅ ይገኙበታል። እንዲሁም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን መልሶ ለማቋቋም የወጣ አዋጅ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ፣ የፌዴራል አሥተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ፣ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤት አዋጅ ፣ የጥብቅና ሙያ አስተዳደር አዋጅና የንግድ ሕግ ሌሎቹ በአማካሪ ምክር ቤቱ አማካኝነት እንዲሻሻሉ የተደረጉ አዋጆች መሆናቸውን ዶ/ር አባድር አስታውቀዋል። ሕጎቹና አዋጆቹ ሲዘጋጁ በሕገ መንግስቱ የተጠቀሱ የሕግ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ እንዲሆኑ የማጣጣም ሥራም አብሮ መሰራቱን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተናግረዋል። በጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ጽህፈት ቤት የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ወርቁ እንደገለጹት ከተሻሻሉትና አዲስ ከተረቀቁት ሕጎችና አዋጆች መካከል ሦስቱ በሕዝብ ተወካዮች ሲጸድቁ አብዛኞቹ ለሚኒስተሮች ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልከዋል። ሌሎች ሁለት አዋጆች ደግሞ የመጨረሻ ረቂቃቸው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል። የሕግ ማሻሻልና ማርቀቅ ሂደቱ በበጎ ፈቃድ በሚያገለግሉ የሕግ ምሁራን የተሠራና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው ሲሉም አቶ እንዳልካቸው ተናግረዋል። የሕግ ማሻሻልና ማርቀቅ ሥራው በአብዛኛው ቢጠናቀቅም የተረቀቁ ሕጎችንና አዋጆችን ተከትለው የሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ያስፈልጋሉ ሲሉ የሕግና ፍትሕ አማካሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤቱ ኃላፊው ዶክተር አባድር መሐመድ ገልጸዋል። በመሆኑም የሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት እነዚህ ደንቦችና መመሪያዎች ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል። አክለውም ሕጎቹን ተረድቶ ለመፈጸም የሚያግዙ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና የህብረተሰቡን የህግ ንቃት የሚያጎለብቱ መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀትም የግድ ነው ብለዋል። ለመመሪያና ደንብ ዝግጅቱም ሆነ ለአቅም ግንባታ ሥራዎቹ አማካሪ ምክር ቤቱ ድጋፍ ለማደርግ ዝግጁ መሆኑንም ዶክተር አባድር አረጋግጠዋል። መንግስት የሀገሪቱ ሕጎች በዘርፉ ባለሙያዎች ባለቤትነት እንዲሻሻሉ ለማድረግ የወሰደው ይህ እርምጃ በኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ አዲስ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አባድር ይህም የሚበረታታ በጎ ጅማሮ መሆኑን አመልክተዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን መልሶ ለማቋቋም የወጣው አዋጅ እንደዚሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በቅርቡ መፅደቃቸው ይታወሳል።