የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ከጳጉሜን 1 ጀምሮ በሕዝብ ይጎበኛል - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ከጳጉሜን 1 ጀምሮ በሕዝብ ይጎበኛል

ነሀሴ 28/2011 የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ከጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት ጉብኝት ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የፍትህ ቀን አስመልክቶ በቀድሞው እስር ቤት ቅጥር ግቢ ኤግዚቢሽን የሚከፈት ሲሆን ለአራት ቀናትም ለሕዝብ ክፍት ይሆናል። ይህ እስር ቤት ከ40 ለዘለቁ ዓመታት ዜጎችን የማሰር፣ የማሰቃየትና እስከ ሕይወት መጥፋት የሚያደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙበት ቆይቶ ከአንድ ዓመት በፊት ተዘግቷል። የአገሪቱ ለውጥ በተበሰረበት ወቅት በዚያ ይፈፀም የነበረው የስቃይ ዘመን ዳግም ላይመለስ በመንግስት ውሳኔ እንዲዘጋና ሙዚየም እንዲሆን መወሰኑም ይታወቃል። ፍትህና ዴሞክራሲ እንዲያብብ በአገሪቱ ታሪክ በተከፈተው አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ሰፊና ሁለንተናዊ ርብርብ በማድረግ የፍትህ ሥርዓቱ በሕገ መንግስቱ መሰረት የሰብዓዊ መብቶችን በማክበርና በማስከበር ረገድ ታሪካዊ እመርታ በመመዝገብ ላይም ይገኛል። በአገሪቱ የህግ የበላይነት በማረጋገጥ፣ አመኔታ የተቸረው የፍትህ ተቋም ለመገባትና አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ዘርፈ ብዙ የሕግ ማሻሻያ ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል። በአገር አቀፍ ደረጃ "ለሕግ ተገዥ ነኝ" በሚል መሪ ሀሳብ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚከበረው የፍትህ ቀን በቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት የተዘጋጀው በዚያ ይፈጸም የነበረውን ክፋት ለማሳወቅና በታሪክ አጋጣሚም እንዳይደገም በታሪክነቱ ለማስቀረት ነው ብሏል። ስቃይ የደረሰባቸው ዜጎች የከፈሉትን ዋጋ ለማሰብ እንዲሁም በወንድሞቻቸው ላይ ግፍ የፈፀሙትን ድርጊታቸውን ለማውገዝ ኤግዚቢሽን መዘጋጀቱንም ጠቁሟል። ለፍትህ ሥርዓቱ መሻሻልና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ኅብረተሰቡ ተሳትፎውን በማጠናከር የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዳር ማድረስ እንደሚገባ ያመለከተው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ስፍራውን እንዲጎበኝ ጋብዟል።