የእግር ኳስ አንድነትን የማጠናከር ሃይል መጠቀም ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የእግር ኳስ አንድነትን የማጠናከር ሃይል መጠቀም ይገባል ተባለ
ነሐሴ 28/211 ስፖርት ሀገራዊ ትስስርንና አንድነትን የማጠናከር አቅም ያለው በመሆኑ በ2012 የውድድር ዓመትም እግር ኳስን ለዚሁ ዓላማ መጠቀም እንደሚገባ ታዋቂው ተጫዋች አዳነ ግርማ ና አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተናገሩ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አደጋ ላይ በመሆኑ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና የተለያዩ የፕሪምየር ሊግ ክለቦችን ያሰለጠነው የአሁኑ የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ስዩም አባተ እንደተናገረው፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከግዜ ወደ ግዜ መልኩን እየቀየረ ና ስጋት እየፈጠረ ይገኛል። እግር ኳሱ ከሰላማዊ ስፖርትነቱ ይልቅ ስርዓት አልበኝነት እየሰፈነበት፤ የፖለቲካ አመለካከት እየተንጸባረቀበት፤ የስፖርት ቤተሰቡን እና ህብረተሰቡን እያሳሰበ ለአደጋም እያገለጠ እንደሚገኝም ነው የተናገረው። በተጠናቀቀው የውድድር አመትም የእግር ኳስ ውድድር ችግር ተባብሶ የቀጠለ መሆኑን የተናገረው አሰልጣኙ፤ ክለቦች ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሄደው መጫወት ያልቻሉበት ወቅት እንደነበረም አስታውሷል። ’’እግር ኳስ ጠላት የሆኑ ሀገራትን እንኳን የሚያስታርቅ ነው” ያለው አሰልጣኝ ስዩም ፤ ጨዋታው ሰላማዊና ጤናማ ፉክክር እንዲኖረው በማድረግ የሀገሪቱን አንድነት ማጠናከር ይገባል ብሏል። ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮችም ጤናማ የእግር ኳስ ፉክክር እንዲኖር ና የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ነው የጠቀሰው። በ2012 የውድድር ዓመትም የእግር ኳስ ቤተሰብ የሚወደውን ጨዋታ ያለጭንቀት የሚያይበትና እግር ኳሱ ከውዝግብ የጸዳ እንዲሆን ምኞቱን የገለጸው አሰልጣኙ፤ የአሰልጣኝነት ሚናውን በአግባቡ ሊወጣ ዝግጁ መሆኑንም ተናግሯል። የቀድሞ የብሄራዊ ቡድንና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች አዳነ ግርማ በበኩሉ ባለፈው የውድድር ዓመት ለእግር ኳስ ጨዋታ አደጋ የሆኑ በርካታ ችግሮች መታየታቸውን ይናገራል፡፡ "ዓመቱ በከባድ ሆኔታ ነው ያለፈው፤ ቡድኖች ሲሸናነፉ ወደ ብሄር ወይም ወደ ማንነት እየተቀየረ እንዲሁም ከሜዳ ውጭ ወጥቶ መጫወት አስቸጋሪ ሆኖ ያለፈበት ነው" ሲልም ዓመቱን አስታውሷል፡፡ እግር ኳስ አንድነት፣ ትብብርና ፍቅር መፍጠሪያ እንጂ የፖለቲካ ማራመጃ አይደለም የሚለው አዳነ፤ እግር ኳስ ውስጥ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን የሚያጸባርቁ ግለሰቦች እየታዩ እንደሆነም ተናግሯል። “የኮትዲቫሩ ድሮግባ እግር ኳስን በመጠቀም ለአገሩ ሰላም ያመጣበት፤ የስፖርቱን ሃያልነት ያሳያል” የሚለው አዳነ፤ ሁላችንም ስፖርቱን ለህብረተሰቡ አንድነት ልንጠቀም ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል። “እንደ ተፈጠረው ችግር የ2011 የውድድር አመት የከፋ አደጋ ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጭም አለመከሰቱ እድለኞች ነን” በማለትም በቀጣይ ዓመት ስፖርቱ ከችግሩ እንፈዲወጣ ከባድ ሥራን ይጠይቃል ብሏል። ምክክርና ውይይት ለስፖርቱ ሰላም መጠናከር ወሳኝ ነው ያለው አዳነ፤ ለእግር ኳስ ሰላም ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።