የኦሮሚያ አትሌቲክስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በአዳማ ከተማ አስተዳደር አሸናፊነት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ አትሌቲክስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በአዳማ ከተማ አስተዳደር አሸናፊነት ተጠናቀቀ
ነቀምቴ ሰኔ 7/2010 በነቀምቴ ከተማ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የኦሮሚያ አትሌቲክስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በአዳማ ከተማ አስተዳደር አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ። በሶስት አትሌቲክስ ዓይነቶች በሩጫ፣ውርወራ እና ዝላይ በተካሄደው ውድድር አዳማ 402 ነጥብ በማግኘት ነው ውድድሩን የበላይ ሆኑ ማጠናቀቅ የቻለው ፡፡ የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና የሰበታ ከተማ አስተዳደር በቅደም ተከተል 315 እና 163 ነጥብ በማምጣት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሚልከሳ ምደጋ በመዝጊያው ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት በነቀምቴ ከተማ የተካሄደው የኦሮሚያ አትሌቲክስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር የአካባቢው ወጣቶች የስፖርቱ ፍቅርና ፍላጎት እንዲኖራቸው ያነሳሳ ነው። የሀገሪቱን ስንደቅ ዓላማ በአለም አደባባይ ከፍ የሚያደርጉ ታዋቂ አትሌቶች በምዕራቡ ክፍል ለማፍራት ሚናው የጎላ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ውድድሩ የአካባቢው ህብረተሰብ የአትሌቲክስ ስፖርት ፍቅር እንዲኖረው ከማነሳሰቱም በላይ ለከተማው ገቢ ምንጭ በመሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉንም አመልክተዋል። የኦሮሚያ አትሌቲክስ ክለቦች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ቱጁባ በበኩላቸው የተካሄደው የአትሌቲክስ ክለቦች ውድድሩ ዓላማ በሀገር ደረጃ በሚካሄደው ተመሳሳይ መረሀግብር ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን መልምሎ ለማዘጋጀት መሆኑን ገልጸዋል። ከቡራዩ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ክለብ በአምስት ሺህና በአስር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው አትሌት ህርጳሳ ነጋሳ በሰጠው አስተያየት ውድድሩ በቀጣይም ለማሸነፍ ብርታት እንደሆነው ተናግሯል። " የአካባቢው አየር ጥሩ ከመሆኑ የተነሳ ያለ ምንም እንቅፋት ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቅቄያለሁ " ያለችው ደግሞ ከአዳማ ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ክለብ የአስር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ራህማ ቲሳ ናት፡፡ ክልሉን ብሎም ኢትዮጵያን እንደ ከዚህ ቀደሙ ለማስጠራት ያዘጋጃት ውድድር እንደሆነም ጠቅሳለች። አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች ሜዳሊያ ለዳኞችና ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ደግሞ የምስክር ወረቀት ከእለቱ እንግዶች ተበርክቶላቸዋል። በውድድሩ በሁለቱም ፆታ ከ600 በላይ አትሌቶች መሳታፋቸው ተገልጿል።