በኢትዮጵያ ከጤና ጋር በተያያዘ ጠንካራ የመረጃ ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል የመረጃ ማእከል ተገነባ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከጤና ጋር በተያያዘ ጠንካራ የመረጃ ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል የመረጃ ማእከል ተገነባ
አዲስ አበባ ነሀሴ 27/2011 በኢትዮጵያ ከጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጠንካራ የመረጃ ስርዓት ለመፍጠር የሚያስችል የኤሌክትሮኒክ መረጃ ማእከል በ12 ሚሊየን ዶላር ወጪ መገንባቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩቱ አስታወቀ። በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰተውን የ'ችኩንጉንያ ወረርሽኝ' ለመከላከል የተቀናጀ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ኢኒስቲትዩት አመልክቷል። ወረርሽኝን ጨምሮ ከጤና ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችሉ ቅድመ ጥንቃቄንና ዝግጅትን ለማድረግ ፈጣንና ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ወሳኝ ነው። እስካሁን ባለው አሰራር ግን እኒህን የመሰሉ መረጃዎች የሚቀርቡት፤ ግምት ላይ በመመስረት ከመሆኑም በላይ የተጠያቂነት አሰራር ስርዓትም እንደሌለው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ይገልፃል። አዲሱ የመረጃ ማእከል ግን ከዚህ ቀደም የነበረውን ግምት ላይ የተመሰረተ መረጃ አሰጣጥ በማስቀረት ትክክለኛና የተጣራ ጤና ነክ መረጃዎችን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ኤባ አባተ ገልፀዋል። ከዚህም ሌላ ጠንካራ የተጠያቂነት አሰራርን በመዘርጋት ተአማኒ የሆነ የመረጃ ምንጭ ለመፍጠርም ያግዛል ብለዋል። የመረጃ ማእከሉ የተገነባው ከቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንና ከኢኒስቲትዩቱ በተገኘ 12 ሚሊዩን ዶላር ወጪ ነው። የመረጃ ማእከሉ ሥራ መጀመር ዛሬ ይፋ በሆነበት ስነ-ስርዓት ላይ የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ከተሞች የተከሰተውን የ'ችኩንጉኒያ' ወረርሽኝ የመከላከል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ኢኒስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ አስታውቀዋል። 'ኤደስ' በምትባል ትንኝ የሚተላለፈው በሽታው በአፋር፣ ሶማሌና ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች እንደዚሁም በድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር መከሰቱን አመልክተዋል። ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የተለያዩ አጋር ድርጅቶች የተውጣጣ ቡድን በየቦታው በመገኘት የተቀናጀ ምላሽ በመስጠት ላይ መሆኑንም ገለፀዋል። በዚህም ከድሬዳዋ ከተማ በስተቀር በሌሎቹ ክልሎች የተከሰተው ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ መከላከል መቻሉን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በድሬዳዋ ከተማ ከሐምሌ ወር 2011 ዓም ጀምሮ በተከሰተው የችኩንጉኒያ ወረርሽኝ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ገልፀዋል። ወረርሽኙን ለመከላከል መንግስት የመከላከያ መድሃኒት ርጭት እያካሄደ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር በየነ የበሽታው ተጠቂዎችም አስፈላጊው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል። እስካሁን ግን በበሽታው ምክንያት ህይወቱን ያጣ የለም ብለዋል። ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ከጤና ተቋማት የሚሰጡ ትእዛዞችን በመተግበር የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል። የችኩንጉኒያ በሽታ ቆላማና ሞቆታማ አካባቢ ላይ “ኤደስ ኤጂፕታይ” በምትባል ትንኝ ንክሻ የሚተላለፍ የትኩሳት ህመም ነው፡፡ የበሽታው ምክንያት ለሆነችው ትንኝ አመቺ መራቢያ የሚሆን የታቆረ ውሃን ማስወገድና አካባቢን ማጽዳት በሽታውን ለመከላከል ይረዳል ተብሏል። በድንገት የሚከሰት ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የአይን መቅላጥ፣ ቁርጥማት፣ ማቅለሽለሽና ትውከት የመሳሰሉ የበሽታ መከሰት መለያ ባህሪዎች መካከል ይገኙበታል።