አገር አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓቱን ለማዘመን እየተሰራ ነው

ነሃሴ 27/2011 በዓለም አቀፍ የመገምገሚያ ነጥቦች በመታገዝ አገር አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሂደትና ስርዓት ግምገማ  ሊደረግ   መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው በወሳኝ ኩነት ምዝገባ አተገባበር ላይ በአገር አቀፍ በሚከወን አጠቃላይ ጥናት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በዚሁ ወቅት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል እንዳሉት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መተግበር ከጀመረበት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ሲያገለግል የነበረው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በ2012 ዓ.ም ይጠናቀቃል። ይህን ተከትሎ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚረዳ ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማዘጋጀት መታቀዱንና ለዚህም የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ስርዓት ሂደት የሚያስቃኝ ሀገር አቀፍ ጥናትእንደሚካሄድ አስረድተዋል። ጥናቱ አጠቃላይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገር አቀፍ ግምገማ የሚካሄድበት መሆኑንና በስድስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል። ጥናቱን ለማካሄድ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልፀው ተቋማቱ ግምገማውን ለማካሄድ ባለሙያዎች እንደሚመድቡም አስረድተዋል። ጥናቱን ተከትሎ የሚዘጋጀውን ዕቅድ ለመተግበር የሚያግዝ በጀት ከመንግስት በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት መገኘቱንም አብራርተዋል። ግምገማው የሚካሄደው በአፍሪካና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመገምገሚያ ነጥቦች መሰረት መሆኑን ጠቅሰው የዛሬው መድረክም የኮሚቴውን ስልጣንና ተግባር እንዲሁም የአገሪቱ ወሳኝ ኩነት ሂደት ላይ ለመወያየት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ዘግይታ የወሳኝ ኩነት ምዝገባን መጀመሯን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ እስካሁን ባለው ሂደት አጠቃላይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ 16 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት ከአራት ሚሊዮን በላይ ኩነቶችን ለመመዝገብ ታቅዶ ክንውኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ወይም የዕቅዱ 48 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል። ክንውኑ ከዕቅድ በታች የሆነው ኅብረተሰቡ ስለ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑና ምዝገባውን ከፍላጎት ጋር ማስተሳሰር ባለመቻሉ መሆኑን በመግለፅ። ምዝገባውን ከፍላጎት ጋር ለማያያዝም የትምህርት ቤት ምዝገባንና የፓስፖርት አገልግሎትን ከልደት ካርድ ጋር ማያያዝ መጀመሩንና ይህም ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል። ህጎችን ከማስፈፀም አንፃርም የነበሩ ክፍተቶች እንደነበሩ ያነሱት አቶ ሙጂብ በቀጣይ ጥናቱ ሌሎች ክፍተቶችንም መለየት የሚያስችል እንደሚሆን ጠቁመዋል። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት ከህጋዊና አስተዳደራዊ ስራዎች ጋር ከመገናኘቱ ባሻገር ከስታትስቲክስ ጋራ የሚገናኙ መረጃዎችን የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። የልደትና የሞት መረጃ  ለኤጀንሲው መሰረታዊ መረጃ በመሆን እንደሚያገለግልና ይህም የህዝብን ብዛት ለመተንበይ ፣ የህዝብ እድገትና የወደፊቱን አቅጣጫ ለማሳየት እንዲሁም ለህዝብ ቆጠራ ቁጥሮችን ለማመሳከር የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል። ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስራ ሲጀመር ጀምሮ ተቋማቸው በትብብር ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው ተቋማቸው በቀጣይም ለሚደረገው ጥናትና ግምገማ መረጃ ለመሰብሰብና ሙያዊ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል። በውይይት መድረኩ ላይ የአፍሪካ ሀገራት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስርዓት የተቃኘ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት 38 አገራት አጠቃላይ ግምገማ ማካሄዳቸው ተገልጿል። ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ስትራቴጂክ ዕቅድ መንደፋቸውንና የድርጊት መርሃ-ግብር መተግበር የጀመሩ መኖራቸውም ተጠቅሷል። በመድረኩ የፓኪስታን የወሳኝ ኩነት ስርዓት ልምድ የቀረበ ሲሆን ለወሳኝ ኩነት ምዝገባ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የባለሙያዎችና በጀት ዝግጅትና መሰል ስራዎች ቀድመው መጠናቀቅ እንዳለባቸውተጠቁሟል። በኢትዮጵያ ካሉ 19ሺህ 20 ቀበሌዎች ውስጥ በ16 ሺህ 900ዎቹ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም