የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን የቶኪዮ ኦሎምፒክ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከካሜሮን ጋር ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን የቶኪዮ ኦሎምፒክ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከካሜሮን ጋር ያደርጋል
አዲስ አበባ ነሀሴ 27/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን የቶኪዮ ኦሎምፒክ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከካሜሮን ጋር በያውንዴ ያደርጋል። ጨዋታው 42 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው አህማዱ አሂጆ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 ይካሄዳል። 29 የልዑካን ቡድንን የያዘው የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ያውንዴ መግባቱን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ለሉሲዎቹ የአዳማ ከተማዋ አጥቂ ሰናይት ቦጋለ ለካሜሮን የሪያል ቤቲሷ አጥቂ ሚካኤላ አባም ግቦቹን ማስቆጠራቸው የሚታወስ ነው። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ግብ በማስተናገዱ ምክንያት የነገው ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብቷል። በ47 ዓመቱ ካሜሩናዊ አሰልጣኝ አለን ጄዩምፋ የሚመሩት የቴራንጋ አንበሶች ከሜዳ ውጪ ያስቆጠሩት ግብ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድላቸውን የሚያሰፋ ነው። ሉሲዎቹ በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም በቶኪዮ ኦሊምፒክ ቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ የኡጋንዳ አቻውን በድምር ውጤት 4 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። አምስት ዙር ባለው የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ጨዋታ በመጨረሻው ዙር የሚቀሩ ሁለት ብሔራዊ ቡድኖች በጥር ወር 2012 ዓ.ም በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ አሸናፊው ቡድን አፍሪካን በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚወክል ይሆናል። ተሸናፊው ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፍ እና በደቡብ አሜሪካ ዞን (ኮንሜቦል) የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ከቺሊ የኦሎምፒክ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታውን አድርጎ ወደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ የማለፍ ዕድሉን የሚወስን ይሆናል። ብራዚል፣ ኔዘርላንድስ፣ ብሪታኒያ፣ ስዊድንና ኒውዚላንድ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ከአዘጋጇ ጃፓን ውጪ መሳተፋቸውን ያረጋገጡ አገራት ናቸው። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር የሴቶች እግር ኳስ ውድድር 12 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።