ቀጥታ፡

በ2012 በኦሮሚያ ክልል በህግ ከተፈቀደለት አካል ውጪ የታጠቀ ኃይል እንዳይኖር እንሰራለን - አቶ አድማሱ

ነሃሴ 27/2011 ''በ2012 በኦሮሚያ ክልል በህግ ከተፈቀደለት አካል ውጪ የታጠቀ ኃይል እንዳይኖር እንሰራለን'' ሲሉ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ  አቶ አድማሱ ዳምጠው ገለጹ። በአዲሱ አመት በሁሉም መስክ ያልተጠናቀቁ ስራዎችን ማጠናቀቅ እና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል። ላለፉት አምስት ቀናት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የ2012 ዓ.ም እቅድና የምክክር መድረክ በትናንትናው እለት ተጠናቋል። ሁለት ሺህ ሰዎች  የተሳተፉበትን የምክክር መድረክ በማስመልከት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በ2012 በጀት ዓመት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ለማጠናቀቀ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የቢሮው ኃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ተናግረዋል። ፈጣን እና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት ህብረተሰቡን የአገልጋይነት መንፈስ በተላበሱ ሰራተኞች በማገልገልና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በፍጥነት ምላሽ መስጠት፤ ከዚህ ቀደም ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ዋነኛ ግብ መሆኑን ጠቁመዋል። ''የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በጥራትና ወጪ ቆጣቢ በሆኑ አሰራሮች ማከናወንና በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር ላይ በትኩረት ይሰራል'' ብለዋል። በጀትን በቁጠባ መጠቀምና ስራዎችን በጥራት ማከናወን ክልሉ የማይደራደርበት ቀይ መስመር እንደሆነ አመልክተዋል። በክልሉ የተጀመረውን የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር የሚከናወንበት አመት እንደሚሆን የጠቆሙት አቶ አድማሱ፤ ''በህግ ከተፈቀደለት አካል ውጪ ማንኛውም የታጠቀ ሃይል በክልሉ ውስጥ እንዳይኖር እንሰራለን'' ብለዋል። የጸጥታ ሃይሉ የህብረተሰቡን ሰላም እንዲጠብቅና ከህብረተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር የአቅም ግንባታና የክትትል ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የህብረተሰቡን ተሳትፎ የማጎልበት ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል። በክልሉ ህግን እየጣሱ መኖር የማይቻል መሆኑን አስገንዝበዋል። ከዚህም በተጨማሪም ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ማሳደግ፣ የዜግነት አገልግሎት መርሃ ግብር ስራዎችን ማጠናከር፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማበረታታት እና ፋይናንስን በአግባቡ መጠቀም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ አድማሱ ጠቁመዋል። የማህበራዊ ልማት ስራዎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማስመዝገብ እና ራስን ለምርጫ ማዘጋጀት የ2012 ዓ.ም ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም