ቀጥታ፡

በአፍሪካ ጨዋታዎች ለተሳተፉ ተወዳዳሪዎች አቀባበል ተደረተገላቸው

አዲስ አበባ  ነሀሴ 27/2011 ሞሮኮ በተካሄደው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ለተሳተፉ  የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች አቀባበል ተደረገላቸው፤ በውድድሩ 23 ሜዳሊያዎችን ይዘው ተመልሰዋል። ውድድሩ ከነሐሴ 13 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በሞሮኮ የተካሄደ ሲሆን ከ54 አገራት የተወጣጡ 6 ሺህ ስፖርተኞች በ26 የስፖርት አይነቶች ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች 181 ስፖርተኞችን በማሳተፍ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስፖርተኛ ያሳተፈች ሲሆን በ12 የስፖርት አይነቶችም ተካፍላለች። በውድድሩ 6 ወርቅ፣ 5 የብርና 12 የነሐስ በድምሩ 23 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ 9ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። 5 የወርቅ፣ 5 የብር ፣ 8 የነሐስ በድምሩ 18 ሜዳሊያዎች በአትሌቲክስ የተገኙ ሲሆን በወርልድ ቴኳንዶ 1 ወርቅ እና ሶስት የነሐስ ሜዳሊያዎች በብስክሌት አንድ ነሐስ ሜዳሊያ ተገኝቷል። የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች በወርልድ ቴኳንዶ፣ አትሌቲክስ፣ ካራቴ፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ጅምናስቲክ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ባድሜንተን፣ ፣ቼስና ቅርጫት ተሳትፋለች። ካራቴ ቅርጫት ኳስ እና ቼስ በሞሮኮው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው አዲስ የተጨመሩ የስፖርት አይነቶች ናቸው። እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች ያስመዘገበችው ከፍ ያለ ውጤት በአህጉራዊ የስፖርት መድረክ አጉልቷታል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸበር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው በአፍሪካ ጨዋታዎች የልዑካን ቡድኑ የነበረው የቡድን መንፈስና ጥንካሬ እንዲሁም ስነ ምግባር የሚያስመሰግነው መሆኑን ተናግረዋል። ስፖርተኞቹ በውድድሩ ስፍራ የነበረውን ሙቀት ተቋቁመው ጠንካራ ፉክክር በማድረግ ውጤት በማስመዝገባቸው መንግስት አስፈላጊውን እውቅና እንዲሰጥ ጠይቀዋል። በሴቶች ግማሽ ማራቶንና 10 ሺህ ሜትር ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት አረንጓዴው ጎርፍ ዳግም በዓለም አቀፍ መድረክ መመለስ መቻሉንም አውስተዋል። በወርልድ ቴኳንዶ የተገኘው ውጤት አበረታች የሚባልና በአጠቃላይ የተገኘው ውጤት በተለያዩ የስፖርት መስኮች ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ እንደሆነም ጠቁመዋል። በስፍራው "የኢትዮጵያ ምሽት" በሚል የሻምበል አበበ ቢቂላ ውለታ እና 82ኛ አመት የልደት በአሉን ለመዘከር ባህላዊ የቡና ማፍላት ፕሮግራም መካሄዱን በማሳያነት ጠቅሰዋል። በወርልድ ቴኳንዶ ከ63 ኪሎ ግራም በታች የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው ታሪኩ ግርማ ከምዕራብና ሰሜን አፍሪካ ተወዳዳሪዎች ፈታኝ ፉክክር እንዳደረገና በአሰልጣኝ ድጋፍና በግል ጥረት ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ተገልጿል። በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችው አትሌት መቅደስ አበበ የቡድን ስራ በመስራት የኬንያ እትሌቶችን ማሸነፍ እንደተቻለ ተናግራለች። በሞሮኮ የነበረው የልዑካን ቡድን ጠንካራ የቡድን መንፈስና ጥንካሬ የታየበት እንደበርም አንስታለች። የአበረታች መድሐኒት ምርምራ ውጤት ቀድሞ ለዓለም አቀፉ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን ባለመላኩ ምክንያት በአፍሪካ ጨዋታዎች ሊሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀናው የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳት ቡድን በውድድሩ ላይ ሳይሳተፍ ተመልሷል። የኢትዮጵያ ክብደት ማንሳትና ሰውነት መገንባት ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለጹት የተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝርና የአበረታች መድሐኒት ምርመራ ውጤት ለዓለም አቀፉ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን መላክ ነበረበት። ይሄም ባለመሆኑ የክብደት ማንሳት ውድድር ከመካሄዱ ከአንድ ቀን በፊት በነበረ የቅድመ ጨዋታ ስብስባ ላይ የስም ዝርዝሩና የአበረታች መድሐኒት ውጤት ቀድሞ ባለመሰጠቱ ምክንያት ዓለም አቀፉ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን ስፖርተኞቹ በውድድሩ ላይ መሳትፍ እንደማይችሉ ገልጿል ብለዋል። የክብደት ማንሳት ስፖርተኞች ውድድር አድርገው ልምምድ ማድረግ የጀመሩት ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በነበረው የአንድ ወር ጊዜ እንደሆነና የአበረታች መድሐኒት ምርምራም ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። ከተገኙ ሜዳሊያዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቼስ ስፖርት በአጠቃላይ ከተሳታፊ አገራት 5ኛ ፣በጠረጴዛ ቴኒስ ከአጠቃላይ ተወዳዳሪ አገሮች በሴቶች ውድድር 6ኛ፣በወንዶች 17ኛ፣በጅምናስቲክ ስፖርት በሴቶች ቡድን 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ግብጽ በ102 ወርቅ 98 የብር 73 የነሐስ በድምሩ 273 ሜዳሊያዎች በማግኘት ውድድሩን በበላይነት ስታጠናቅቅ ናይጄሪያ በ46 የወርቅ 33 የብር 48 ነሐስ በድምሩ 127 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ደቡብ አፍሪካ በ3 የወርቅ በ26 የብር እና በ25 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ በ87 ሜዳሊያዎች ሶስተኛ የወጣች ሲሆን አዘጋጇ አገር ሞሮኮ በ31 ወርቅ በ32 የብር በ46 የነሐስ በድምሩ በ109 ሜዳሊያዎች አምስተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች። 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እ.አ.አ በ2023 በጋና አስተናጅነት የሚካሄድ ይሆናል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም