በአንድ ግለሰብ ወይም ብሔር በጎነት ብቻ አገርን ማሻገር አይቻልም - የጋሞ አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ግለሰብ ወይም ብሔር በጎነት ብቻ አገርን ማሻገር አይቻልም - የጋሞ አባቶች
ነሐሴ 27/2011 በአንድ ግለሰብ ወይም ብሔር በጎነት ብቻ አገርን ማሻገር እንደማይቻል የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ። ሽማግሌዎቹ የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቆ ለማስቀጠል መላው ኢትዮጵያዊያን በጎ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የጋሞ አባቶች ትናንት በተካሄደው ሰባተኛው የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት ስነ-ስርዓት ግጭትን በባህላዊ መንገድ በማስቆም በተግባር በተጫወቱት ሚና የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። የጋሞን የአገር ሽማግሌዎች የወከሉት አባቶች የሽልማቱ አዘጋጆች የሚያውቁት በ2010 ዓ.ም በአርባ ምንጭከተማ እርጥብ ሳር በመያዝ ለቀውስና ለግጭት የተነሱ ወጣቶችን የታደጉበትን ሁነት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። ይሁንና በሺህዎች የሚቆጠሩ የጋሞ አባቶች ከዛ ሁነት በፊትም ሆነ በኋላ ጥይት በሚተኮስበትና ጦር በሚወረወርበት አስቸጋሪ ቅፅበት እየተገኙ ውድመት ሊያስከትሉ የሚችሉ በርካታ ግጭቶችን በሠላም መፍታታቸውን አስረድተዋል። የተበረከተላቸውን ሽልማትም ለጋሞ ሕዝብና ለአባቶች ታዛዥ ለሆኑት የጋሞ ወጣቶች የተበረከተ ነው ብለዋል። 'በአንድ ግለሰብ ወይም ብሔር ብቻ አገርን ማሻገር አይቻልም' ያሉት አባቶች፤ ሀብት እየወደመና ባንዲራ እየተቃጠለ አገርን አንድ አድርጎ መምራት እንደማይቻል ተናግረዋል። የአገርን አንድነት ጠብቆ ለማስቀጠል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎ መሆን እንዳለበት መክረዋል። ለኢትዮጵያ የተለየ ባለውለታና ክፉ አድራጊ ሕዝብ እንደሌለለ ገልጸው፤ 'የማንገፋፋባት፣ የማንናናቅባትና የማንጣላባት፤ እኩል የታሪክ ባለቤት የሆንባት አገር መገንባት ይገባናል' ሲሉም ተናግረዋል። ከጋሞ የአገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ አንጅሎ አርሾ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የጋሞ ሕዝብ ማንኛውንም ግጭት የሚፈታበት ለዘመናት የዳበረ ባሕላዊ ስርዓት ያለውና ለአገር ሉዓላዊነት የሚተጋ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም በጋሞ ሕዝብ መካከልም ይሁን በጎረቤት አካባቢዎች ግጭቶች ሲከሰቱ በተግባር ሲፈታ መቆየቱን አውስተዋል። በአንድ ግለሰብ ወይም ሕዝብ ብቻ ሠላምን ማምጣት ስለማይቻል፣ በጎ ሰዎችንና በጎ ብሄረሰብን በመጠቀም በሌሎች ላይ መስራት ይጠበቃልም ብለዋል።