ለግማሽ ሚሊዮን ሰነድ አልባ ይዞታዎች ህጋዊ ሰነድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ለግማሽ ሚሊዮን ሰነድ አልባ ይዞታዎች ህጋዊ ሰነድ ተሰጠ
ነሐሴ 27/2011 በመላ ሀገሪቱ ሰነድ አልባ ይዞታዎችን ህጋዊ ለማድረግ በተከናወነው ስራ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለይዞታዎቻቸው ህጋዊ ሰነድ መስጠቱን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ አሁንም 500 ሺህ የሚሆኑ ሰነድ አልባ ይዞታዎች መኖራቸው ተገልጧል ። በሚኒስቴሩ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ብዙአለም አድማሱ ለኢዜአ እንደተናገሩት ሰነድ አልባ ይዞታዎችን ህጋዊ የማድረጉ ስራ የተከናወነው በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ነው፡፡ ሰነድ አልባ ይዞታዎችን ህጋዊ በማድረግ ከተማ አስተዳደሮች ያከናወኑት ተግባራት መልካም ቢሆንም ከተቀመጠው እቅድ አኩያ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ አልተቻለም ብለዋል፡፡ ቀሪ 500 ሺህ የሚሆኑ ሰነድ አልባ ይዞታዎች ህጋዊ አልተደረጉም ያሉት ቢሮ ሃላፊው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ህጋዊ አሰራሮችን በመከተል ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ ሰነድ አልባ ይዞታዎችን ህጋዊ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የአማራ ክልልና የአዲስ አበባ መስተዳድር መሆናቸውንም የቢሮ ሃላፊው ገልጸዋል፡፡ ክልሎች የህግ ማእቀፉን መነሻ በማድረግ በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ ይዞታዎችን ሙሉ በሙሉና በከፊል እንዲፈርሱ እንዲሁም በቅጣት ጭምር እንዲስተካካሉ የማድረግ ስራ አከናውነዋል ። አገራዊ የሊዝ አዋጁን መሰረት በማድረግ በ456 ሺህ ህገ ወጥ ይዞታዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የማስትካከል ስራ መከናወኑን ተናግረዋል ። ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታን በመቆጣጠርና በመከላከል ረገድ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወጥ በሆነ መንገድ አለመስራታቸው ግን በክፍተትነት አንስተዋል ። ለአብነትም በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማና ዙሪያው 17 ሺህ 360 ያህል ህገ-ወጥ ግንባታ መፈጸሙን አመልክተዋል፡፡ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የፈጸመ አካል እንዲሁም ሃላፊነቱን ያልተወጣ የከተማ አስተዳደር አመራር ከ7 እስከ 14 አመት በእስራት እንደሚቀጣ በሊዝ አዋጁ መደንገጉንም ጠቁመዋል፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት በከተሞች የህገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ እየገዘፈ መምጣቱን ጠቁመው በአመራሩ ጥረት ብቻ ችግሩን መቅረፍ የማይቻል በመሆኑ የህብረተሰቡ ተሳትፎና ቁጥጥር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ፈንታ ደጀኔ በበኩላቸው የክልሉ የመሬት ማኔጅመንት ዘመናዊ አለመሆን ለህገ-ወጥ የመሬት ወረራ በር መክፈቱን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የመሬት ወረራ መስፋፋት ዜጎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሀብቱን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ማድረጉን ጠቀሙው ችግሩን ለመቅረፍ ሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል ፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ሚኒስቴሩ ከክልሎች ጋር የጀመረውን የምክክር መድረክ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ምክክሩ ወደ ህዝቡ ጭምር ወርዶ አመራሩ የህዝቡን ተሳትፎ በማስተባበር ችግሩን ስር ነቀል በሆነ አግባብ መፍታት እንዲቻል ርብርቡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡