ቀጥታ፡

የስራ እድል ፈጠራ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ተባለ

ነሃሴ 26/2011 የስራ እድል ፈጠራ በጥናት ላይ የተመሰረተና ማምረትን ማእከል ያደረገ ካልሆነ የታለመለትን አላማ ማሳካት አይችልም ሲሉ አንድ የኢኮኖሚ ምሁር ተናገሩ፡፡ የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ ለሥራ እድል ፈጠራ ውጤታማነት የአመራር ሚና ወሳኝ  ነው ብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ዶክተር አጥላው አለሙ እንዳሉት፤ ከዚህ በፊት መንግስት ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ የሚያቀርበው ብድር መልካም  ቢሆንም ስራዎቹ ላይ የአዋጭነት ጥናት አለመካሄዱ የገንዘብ ብክነትን አስከትሏል፡፡ ለወጣቶቹ የሚቀርቡ ስራዎችን በመለየት፤ አዋጭነታቸውንና የገበያውን ሁኔታ ማጥናት፣ በቂ የቴከኒክ ድጋፍ መስጠትና ራሳቸው አጥንተው ካመጡም አዋጭነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ የተበደሩትን ገንዘብ  በአግባቡ ካልተጠቀሙ የኑሮ ውድነት ተጽእኖን ያሳድራል ያሉት ዶክተሩ፤ ገንዘብ ያለ ጥቅም ባክኖ ሲቀርም ለግሽበት መንስኤ እንደሚሆን ነው የገለፁት፡፡ ሃገሪቱ እዳ ውስጥ የገባችው ብዙ እቃዎችን ከውጪ ስለምታስገባ  ነው ያሉት ዶክተር አጥላው፤ በትናንሽ ማኑፋክቸሪንግ በማምረት ለትልልቆቹ መሰረት መጣል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም ተገቢው ድጋፍ አለመደረጉን ገልጸው፤ ቴክኖሎጂን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ማላመድ እና አመሳስሎ በመስራት፣ የመገልገያ እቃዎች(በፈርኒቸር)፣ የግንባታ እቃዎችና ኬሚካሎችን በሃገር ውስጥ ለመስራት ያለውን ሙከራ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ  ወይዘሮ አቦዘነች ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለፁት በጥቃቅንና አነስተኛ የሚፈጠሩ የስራ ዘርፎች በዋናነት የከተማ ድህነትን ለመቅረፍና ዜጎች ከሃገሪቱ ሃብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው፡፡ አብዛኛው የከተማ ነዋሪ በድህነት ላይ ያለ በመሆኑ፤ጉልበቱን እና ግዜውን አስተባብሮ  ማህበራዊ ዋስትናውን በማረጋገጥ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ  ማሳደግ ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖረው  ታስቦ ጥቃቅንና አነስተኛ ስትራተጂ መቀረፁንም ነው  ቡድን መሪዋ የተናገሩት፡፡ “ዘርፉ ከብዙ ሴክተሮች የሚገናኝ እንደመሆኑ አንድን ሰው ወደ ዘርፉ አስገብቶ ውጤታማ ማድረግ ትኩረትን ፣እውቀትና ብቃትን የሚጠይቅ ነው”ያሉት ቡድን መሪዋ፤ የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ ባለሙያዎች የትምህርት ዝግጅት የሚታየውን ክፍተት ለመቀየር ስልጠና  እንዲያገኙ እየተመቻቸ ነው ብለዋል፡፡ ዜጎችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚፈለገው ካፒታል አለመኖር፣ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት  ሰልጣኞችን በቂ ክህሎት የማስጨበጥ  ክፍተት፣ የአመራሮች መቀያየርና የባለሙያ ፍልሰት የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ አፈፃፀም  ከክልል ክልል እንደሚለያይ ተናግረው “መረጃ በአግባቡ ያለመያዝ፣ በአንዳንድ ክልሎችም ለጠፋው ህይወትና ንብረት ካሳ ነው “የሚል ከአመራር ጭምር የሚንጸባረቅ በመሆኑ ብድሩን ለማስመለስ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአንፃሩ በአማራ ክልል አንድ ሰው ብድር ለመውሰድ የሚያስፈልገውን ቅድመ ሁኔታ ተከትሎ በመስራቱ የተበደሩትነ ገንዘብ ለማስመለስ አለመቸገሩን የገለጹት ወይዜሮ አቦዘነች፤   ተዘዋዋሪ ፈንዱ አተገባበሩ ላይ ክትትልና ቁጥጥር ከተደረገ ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በተግባር ታይቷል ብለዋል፡፡ “የስራ እድል ፈጠራው የአመራር ቁርጠኝነትም ያስፈልገዋል” ያሉት ቡድን መሪዋ፤ አመራሩ በሰራባቸው አካባቢዎች ዜጎች በአዳዲስ ስራዎች ተጠቃሚ እንደሆኑና  አመራሩ  ችላ ባለበት  ደግሞ ዝቅተኛ አፈፃፀም መታየቱን ነው የጠቀሱት፡፡ የስራ እድል ፈጠራው አመለካከትን እና የስራ ባህልን በመቀየር ዜጎችን የሙያ ባለቤት በማድረግ በጎ አስተዋጽኦ እንደነበረው የተናገሩት ወይዘሮ አቦዘነች፤ በተያዘው በጀት አመትም የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታና የተፈጥሮ ሃብትን  ግምት ውስጥ በማስገባት  አዳዲስ የስራ እድሎችን ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል፡፡ መንግስት የመደበው 10 ቢሊዮን የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ብቻ በሃገሪቱ ያለውን ወጣት የኢኮኖሚ ችግር አይቀርፍም ያሉት የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ፤ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ በተጨማሪ ክልሎችም በጀት እየመደቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የብድር አመላለሱ እንደሚሰራው ፕሮጀክቶች እንደሚለያይ ገልፀው “የስራቸውን ውጤት እያሳዩ ሲሄዱ ነው የሚከፍሉት፤ ይህም የብድር ውሉ ግዜ ይወስነዋል” ብለዋል፡፡ ብሩ ሲሰራጭ በቂ ስልጠና ባለመሰጠቱና በአጣዳፊ ሁኔታ የተሰጠ በመሆኑ ውጤታማ ያልሆኑ ወጣቶች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት አቶ ሃጂ፤ ብድሩ ከመሰራጨቱ በፊት በቂ ጥናት አለመደረጉ፣ የወረዳዎችን የስራ አቅምና ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም  በቂ ስልጠና  ያለመስጠት ክፍተት ታይቶ ነበርም ብለዋል፡፡ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በየአመቱ የብድር ሁኔታን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፤ ተዘዋዋሪ ፈንዱ በክልሎች ምን ያህል ጥቅም ላይ እንደዋለ ና የብድር መመለስ ምጣኔ በቅርቡ ምክክር እንደሚደረግበት ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት በከተሞች ለ2 ሚሊዮን 634 ሺህ 496 ሰዎች፤  በገጠር ደግሞ ለ2 ሚሊዮን 826 ሺህ 749 ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩን ከግብርና ሚኒስቴርና ከፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግበ ዋስትና ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም