በእውነታ ላይ የተመሰረተ መረጃ ልማቱን ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
በእውነታ ላይ የተመሰረተ መረጃ ልማቱን ያግዛል
ነቀምቴ ሰኔ 7/2010 ሴክተር መስሪያ ቤቶች በእውነታ ላይ የተመሰረተ መረጃ በመሰብሰብ ለልማቱ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ የነቀምቴ ቅርንጫፍ ገለፀ። ከ200 በላይ የሴክተር መስሪያ ቤቶች የመረጃ አያያዝ ባለሙያዎች የተዘጋጀ የአራት ቀናት ስልጠና ትናንት በነቀምቴ ከተማ ተጀምሯል፡፡ በስልጠናው መክፈቻ ላይ የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ በላይ አቦማ እንደገለፁት ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃ በመሰብሰብ ለመንግስትና ለህዝብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ስኬቱም ሆነ ክፍተቱ የሚመዘነው ሴክተር መስሪያ ቤቶች በሚያቀርቡት መረጃ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑ መረጃው በአግባቡ የተደራጀ፣ በእውነት ላይ የተመሰረተና ጥራቱን የጠበቀ በማድረግ ልማቱን ማገዝ ከባለሙያዎች እንደሚጠበቅ ሃላፊው ጠቁመዋል። የስልጠናው ዓላማም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ትክክለኛ መረጃን ለመንግስትና ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችላቸውን የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ጽህፌት ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሽ ሃይሉ እንደተናገሩት ስልጠናው የመረጃ አያያዝና አቀራረብ ስርዓት የሀገሪቱን ብሎም የህብረተሰቡን እጣ ፈንታ የሚወስን በመሆኑ ባለሙያዎች ለመረጃ ጥራት ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ። ከተሳታፊዎች መካከል የኑኑ ቁምባ ወረዳ የእቅድና ግምገማ ባለሙያ ወይዘሮ መሰረት ጌታቸው በሰጡት አስተያየት ስልጠና በመረጃ አያያዝ ዙሪያ የነበረባቸውን ክፍተት በመሙላት በተሻለ መልኩ ለመስራት እንደሚያግዛቸው ገልፀዋል፡፡