ቀጥታ፡

የክልሉን ህዝቦች በእኩልነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ

ሀዋሳ ኢዜአ ነሐሴ 25/2011  የክልሉን ህዝቦች በእኩልነትና በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ዛሬ የተሾሙት አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ የሾማቸው አቶ ርስቱ ይርዳው በዚህ ወቅት የክልሉ መንግስትና ደኢህዴን ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ብልሀትን የሚጠይቁና ፈርጀ ብዙ የሆኑ ውሰብስብ ችግሮች በገጠሟቸው ወቅት ይህን ኃላፊነት መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም አስተዋይና ኩሩ የሆኑት የክልሉን ህዝቦች ለመምራት በመታደላቸው ክብርና ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል ፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል መላው የክልሉን ህዝቦች በእኩልነትና ቅንነት በተመላበት መንፈስ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን  አስታውቀዋል፡፡ አቶ ርስቱ እንዳሉት የደቡብ ክልል የብዝሀነት ፣ የአብሮነት ፣ የመቻቻልና በጋራ የመልማት እሴት ያዳበረ ፣እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ለልማት የተመቸ ውብ ስነ ምህርዳር ባለቤት ነው፤ ይህን በመጠቀም በአጭር ጊዜ የመበልፀግ እድል አለው ፡፡ ክልሉ ሲደራጅም ያሉትን የብልፅግና መሰረቶች በማዋሀድ ለጋራ ልማት እንዲውሉና ህዝቦቹ ያሏቸው ተመሳሳይ ሥነ ልቦናና ትስስር እንዲጎለብት ፣ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውንና ተደማጭነት ለማሳደግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ ቀጣይነት ያለው የመሰረተ ልማትና የገበያ ትስስር እየጎለበተ መምጣቱን ፣ የተማረ የሰው ኃይል ማሳደግ መቻሉን ፣ የህዝቦች ህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከሩን አውስተዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በነበሩ የአደረጃጀት ፤ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ጥያቄዎች የተነሳ በተከሰቱ አለመረጋጋቶች በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ በክልሉ የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስና መልሶ የማቋቋም ሥራ ከመላው ህዝብ ጋር በመቀናጀት የሚሰሩት ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ አስታውቀዋል ፡፡ በክልሉ ባጋጠሙ የፀጥታ ችግሮች የተነሳ የግብርና ምርታማነት ፣የገጠርና ከተማ ኢንቨስትመንት ፣ የኢንተርፕራይዞች ልማትና የአገልግሎት ዘርፉ ተቀዛቅዞ መቆየቱን ያመለከቱት አቶ ርስቱ ይህንን በፍጥነት ለማሻሻል ብሎም የኑሮ ውድነትንና የወጣቶች ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ አቶ ርስቱን ለምክር ቤቱ አባላት በዕጩነት ያቀረቡት የደኢህደን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ናቸው። አቶ ርስቱ ይርዳው በጉራጌ ዞን ከወረዳ እስከ ዞን አስተዳደሪ ና በደቡብ ክልልና በፌዴራል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የስራ ኃላፊነት ቦታዎች  ማገልገላቸውን አቶ ሞገስ ገልፀዋል ፡፡ ምክር ቤቱም ሹመቱን ተቀብሎ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ክልሉን እንዲመሩ  በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም