ቀጥታ፡

ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርን በዘላቂነት ለመፍታት የአጠቃቀም ስርዓት ሊኖር ይገባል ተባለ

ነሀሴ 25/2011 በኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርን በዘላቂነት ለመፍታት ግኙቱን ማሳደግና ለአጠቃቀሙ ስርዓት ማበጀት ይገባል ተባለ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ የሚያተኩሩ ፖሊሲና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጾ ካለፈው ዓመት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መኖሩን አስታውቋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች የኢኮኖሚ ዕድገት ስታስመዘግብ መቆየቷ በተደጋጋሚ ይገለጻል። ከዕድገቱ ጋር አብሮ የሚሄድ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አለመኖር ደግሞ እንደ ችግር ሲነሳ የቆየ ሲሆን ለእጥረቱ ቀዳሚው ምክንያት በህገ-ወጥ መንገድ ገበያው ላይ የሚዘዋወረው የውጭ ምንዛሪ እንደሆነ ይነሳል። መንግስት በተጠናቀቀው 2011 በጀት ዓመት ባደረገው ቁጥጥር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ የውጭ አገራት ገንዘብ መያዙን ሲገልጽ ነበር። በተጨማሪም ከተቀመጠው ተመን በላይ የውጭ አገር ገንዘብን ሲመነዝሩ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን ተቋማትም እስከ ማሸግ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ ወስዷል። የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ህጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢ ቢሆንም በዘላቂነት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት የወጪ ንግድ ላይ ማተኮር ዋነኛው መፍትሄ ነው ይላሉ። መንግስት የወጪ ንግድን ከማበረታታት ባለፈ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ላይ የፖሊሲ ፍተሻ ማድረግ እንዳለበትም ጨምረዋል። ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ሸቀጦች 80 በመቶ እሴት ያልተጨመረባቸው የግብርና ውጤቶች መሆናቸውን በመጠቆም ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከዲያስፖራ ወደ አገር ውስጥ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) ሌላኛው የውጭ ምንዛሪ ግኝት አማራጭ እንደሆነ የሚገልጹት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ኢትዮጵያ በዓመት የምታገኘው አራት ቢሊዮን ዶላር ከጎረቤት አገር ግብጽ 26 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ አማራጮችን በማየት እጥረቱን መፍታት እንደሚቻል መክረዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው እየተደረገ ባለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ መሆኑን አስታውቀዋል። በመንግስት ተይዘው የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል ማዘዋወር፣ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ እንደ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ሌሎችም አዳዲስ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል። የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ የአቅርቦት ችግር ሲኖር ህገ-ወጥ ድርጊት እንደሚፈጠር በመግለጽ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት አቅርቦቱን መሻሻል ዋነኛው መፍትሄ መሆኑን ይገልጻሉ። በመሆኑም አቅርቦቱን ከማሻሻል ጎን ለጎን ህገ-ወጥ ዝውውርን ለመከላከል አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል። በ2011 በጀት ዓመት ከረጂዎች ከፍተኛ ዶላር መገኘቱን ገልጸው ይህም የመጠባባቂያ ክምችትን ከፍ ለማድረግ አግዟል ብለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ዋነኛ ትኩረት በማድረግ አጠቃቀሙ ላይ የሚያተኩሩ ፖሊሲና መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረጉን እንደሚቀጥልና በአሁኑ ወቅት ካለፈው ዓመት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መኖሩን አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ድንበር አቋርጠው በአየር ወይም በየብስ የውጭ አገራት ገንዘብ ይዘው ሊወጡ ሲሉ የሚያዙ ግለሰቦች ቁጥር በርካታ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም