ቀጥታ፡

በድሬዳዋ 400 ሕገ ወጥ ቤቶች ፈረሱ

ድሬዳዋ ነሐሴ 25 / 2011 የድሬዳዋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዙሪያ የተገነቡ 400 የሚጠጉ ሕገ ወጥ ቤቶችን ማፍረሱን አስተዳደሩ አስታወቀ። የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ''ሕገ-ወጥ ግንባታ የማፍረስና የመሬት ወረራን የመከላከሉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል''ብለዋል። የአስተዳደሩ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንዳመለከተው በአስተዳደሩ የተቋቋመው አፍራሽ ግብረ-ኃይል ሕገ-ወጥ ቤቶችን አፍርሷል፡፡ ቤቶቹ ከፈረሱ በኋላ ምሽት ላይ የተገነቡ 11 ቤቶችም እንዲፈርሱ አድርጓል፡፡ ከሕገ-ወጥ ቤቶቹ የፀዳው ሥፍራ ''በዘላቂነት ጥበቃ'' ይደረግለታል ብሏል፡፡ አየር ማረፊያው ባለፈው ሣምንት የችግሩን አሳሳቢነት በመግለጽ አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ ሥራውን ለማቆም እንደሚገደድ አስታውቆ እንደነበርም አስታውሷል፡፡ የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ በአስተዳደሩ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ቤቶቹ የፈረሱት በአየር ማረፊያው ሥራ ላይ ጫና በመፍጠራቸው መሆኑንና ሲፈርሱም ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ''መሬትን በመቀራመትና ችግር እየፈጠሩ ያሉት ቤት የሌላቸው ሳይሆኑ ደላሎች ናቸው'' ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ባዐቤቶቹ እንዲያፈርሱ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡ እንደ አፈ-ጉባዔዋ ገለፃ በከተማዋ ሕገ-ወጥ መሬት ወረራንና ግንባታን መከላከል በማጠናከር ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረና ሥራ በመፍጠር ልዩ ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል፡፡ ለሥራም ልዩ ትኩረት በመስጠት በአስተዳደሩ የሚታየውን የሥራ ፈጠራና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡ አስተዳደር ቤት ለሌላቸው ወገኖች ከሌሎች አካባቢዎች የቀሰማቸውን አማራጭ የቤት ግንባታመንገዶችን እንደሚተግብር አፈ ጉባዔው ተናግረዋል፡፡ ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች ድንጋይ በመወርወርና ጎማ በማቃጠል ተቃውሟቸውን ሰሞኑን ገልጸዋል፡፡ ቤታቸው ከፈረሰባቸው ሰዎች መካከል ወይዘሮ ፋይዛ ዩሱፍ ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ቤታቸው በመፍረሱ ሜዳ ላይ ለመኖር መገደዳቸውን ገልጸዋል። አስተዳደሩ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡ በከተማዋ ባለፉት 17 ዓመታት እስከ 25 ሺህ የሚገመቱ ሕገ-ወጥ ቤቶች በተለይ በቅርብ ዓመታት ለልማት በሚውሉና በዋሉ ተቋማት አካባቢዎች መገንባታቸውን የቢሮው መግለጫ ያስታውሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም