ቀጥታ፡

የአፍሪካ ጨዋታዎች ዛሬ ይጠናቀቃሉ

ከነሐሴ 25/ 2011  ከነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በሞሮኮ ሲካሄድ የቆየው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል። 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ከ54 የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ ስድስት ሺህ ስፖርተኞች በ26 የስፖርት አይነቶች ሲሳተፉ የቆዩ ሲሆን የስፖርተኞች ተሳታፊ ብዛት በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛው የሚባል ነው። ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው ውድድር ዛሬ በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚገኘውና 52 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው የፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ 45 በሚካሄድ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ፍጻሜውን ያገኛል። በሁለቱም ጾታዎች የቡድን ቴኒስ እንዲሁም በወንዶች የመረብ ኳስ የፍጻሜ ጨዋታዎች በውድድሩ የመጨረሻ ቀን የሚደረጉ ውድድሮች ናቸው። ኢትዮጵያ 188 ስፖርተኞችን በ13 የስፖርት አይነቶች በማሳተፍ በውድድሩ ተሳትፎዋ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የስፖርተኛ ቁጥር ማሳተፍ ችላለች። ወርልድ ቴኳንዶ፣ አትሌቲክስ፣ ካራቴ፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ጅምናስቲክ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ባድሜንተን፣ ክብደት ማንሳት፣ ቼስና ቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። ካራቴ ቅርጫት ኳስ እና ቼስ በሞሮኮው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው አዲስ የተጨመሩ የስፖርት አይነቶች እንደሆኑም ይታወቃል። ኢትዮጵያ በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች 6 ወርቅ፣ 5 የብርና 12 የነሐስ በድምሩ 23 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። 5 የወርቅ፣ 5 የብር ፣ 8 የነሐስ በድምሩ 18 ሜዳሊያዎች በአትሌቲክስ የተገኙ ሲሆን በወርልድ ቴኳንዶ 1 ወርቅ እና ሶስት የነሐስ ሜዳሊያዎች በብስክሌት አንድ ነሐስ ሜዳሊያ ተገኝቷል። ኢትዮጵያ ከናይጄሪያና ኬንያ በመቀጠል በአትሌቲክሱ ብዙ ሜዳሊያዎችን ያገኘች አገር ሆናለች። ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2015 በኮንጎ ብራዛቪል በተካሄደው 11ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በ7 ወርቅ  በ5 ብር በ10 የነሐስ ድምሩ 22 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ስምንተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት ከተካሄደው ውድድር አንጻር ኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ዝቅ ብላለች። ያስመዘገበችው የወርቅ ሜዳሊያ ብዛት በአንድ ዝቅ ብሏል፤ የብር ሜዳሊያው ተመሳሳይ ሲሆን በነሐስ የሁለት ሜዳሊያ ጭማሪ በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት በአንድ መሻሻሉን ማየት ይቻላል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች 7 ወርቅ ያገችበት የኮንጎ ብራዛቪሉ ውድድር በአፍሪካ ጨዋታዎች ብዙ ቁጥር ያለው የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ስድስቱ በአትሌቲከስ አንዱን በወርልድ ቴኳንዶ የተገኙ ናቸው። የአፍሪካ ጨዋታዎች እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1965 በኮንጎ ብራዛቪል መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ12ቱም ውድድሮች የተሳተፈች ሲሆን በአጠቃላይ በውድድሮቹ 37 ወርቅ 44 ብር 64 ነሐስ በድምሩ 145 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች። የዛሬ የፍጻሜ ጨዋታዎችን ሳይጨምር በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ግብጽ በ101 ወርቅ፣ በ97 የብር፣ በ72 ነሐስ በድምሩ 270 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የበላይነቱን ስትይዝ ናይጄሪያ በ46 ወርቅ በ33 የብር በ47 የነሐስ በድምሩ በ126 ሜዳሊያዎች ተከታዩን ደረጃ ይዛለች። ደቡብ አፍሪካ በ36 ወርቅ፣ በ26 የብር በ25 ነሐስ በድምሩ 87 ሜዳሊዎችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን አዘጋጅ አገር ሞሮኮ በ26 የወርቅ በ36 የብር በ46 የነሐስ በድምሩ 107 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በአጠቃላይ በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ከተሳተፉት 54 አገራት መካከል 42ቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ችለዋል። የአፍሪካ ጨዋታዎች(የአፍሪካ ኦሎምፒክ) የሚባለው ውድድር እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠረ በ2020 በቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ እንደ ማጣሪያ ውድድር የሚያገለግል ነው። ግብጽ፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ እስካሁን በተካሄዱት 12 የአፍሪካ ጨዋታዎች ብዙ ሜዳሊያ በመሰብሰብ በቅደም ተከተል ከአንድ አስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም