ለነገዋ ኢትዮጵያ ስኬት የሚሰሩ ወጣቶች ሊደገፉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለነገዋ ኢትዮጵያ ስኬት የሚሰሩ ወጣቶች ሊደገፉ ይገባል
ነሐሴ 25/2011 ዘመን ተሻጋሪ ሃሳብ ሰንቀው ትውልድ ለማነጽ የሚሰሩ ወጣቶች ሊደገፉ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ። ወጣቶች የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ የህይወት ክህሎት ስልጠና የመስጠት ራዕይ ያለው 'ኢምፓወሪንግ ኔክስት ጄኔሬሽን ኢትዮጵያ' የተሰኘ ድርጅት ትናንት ማምሻውን በአዲስ አበባ ተመስርቷል። ድርጅቱ በአራት ወጣቶች የተመሰረተ መንግስታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎት ተቋም ነው። ድርጅቱ ከ6 እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ታዳጊና ወጣት ተማሪዎች በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች የህይወት ክህሎት ስልጠናና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገልጿል። ከሱስ ነጻ የሆነ ወጣትና ሰላማዊ ማህበረሰብ መፍጠር፣ ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ወጣቱ በማህበረሰቡ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው መስራትም ከድርጅቱ ራዕዮች መካከል ናቸው። በምስረታው ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ኢምፓወሪንግ ኔክስት ጄኔሬሽን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ሆኖ የነገዋን ኢትዮጵያ እንዴት መስራት እንደሚቻል የሚያሳይ ዘመን ተሻጋሪ ሀሳብ የያዘ ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ዕቅዱ ወጣቶች በኢትዮጵያ ለውጥ ውስጥ ያልተነበቡ ገጾችን የመግለጥ አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ነው ሲሉም ነው የተናገሩት። "ወጣቶች የነገዋን ኢትዮጵያ የመስራት አቅማቸው እጅግ ከፍተኛ ነው" ያሉት ሚኒስትሯ የድርጅቱ ህልም ኢትዮጵያን የሚቀይሩ ባለ ራዕይ ወጣቶች በስፋት እንዳሉ የሚያመላክት ነው ብለዋል። ወጣቶቹ ዘላቂ ሰላምን እንዴት መገንባት እንደሚቻል በደምብ ገብቶቸዋል ሲሉም ሚኒስትሯ አሞካሽተዋቸዋል። ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተልዕኮዎች አንዱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ ባለው መስጠትና ማካፈል ዘላቂ ሰላምን መገንባት እንደሆነና የድርጅቱ ስራም የሚኒስቴሩን ተልዕኮ ለማሳካት አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል። የኢምፓወሪንግ ኔክስት ጄኔሬሽን ኢትዮጵያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወጣት አልዓዛር ዘላለም ወጣቱ በአስተሳሰብ ለውጥ አመጥቶ ቁሳዊ ድህነትን እንዲያሸንፍ ድርጅቱ በትኩረት እንደሚሰራ ይገልጻል። ወጣቶች ያለባቸውን ችግር በእርዳታ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ራሱን ችሎ ነገ ብቁ ዜጋ እንዳይሆን መሰናክል እንደሚፈጥርበትና ከእርዳታ ይልቅ ወጣቱ በአስተሳሰብ ልቆ ችግሩን መፍታት የሚችልበት መንገድ ማሳየት ባለ ራዕይ ወጣት ለመፍጠር በር ይከፍታል ይላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንዴት እንፍታቸው? ችግሩን ለመፍታት ከማን ከምን እና ከየት ይጀመር? ችግርን እንዴት እናሸንፈው? ችግርን አልፎ መፍትሄ ማበጀት የሚችል ትውልድ እንዴት እንፍጠር? የሚሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ድርጅቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መቋቋሙን አመልክቷል። የኢምፓወሪንግ ኔክስት ጄኔሬሽን ኢትዮጵያ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወጣት አርዕስት አብይ በበኩሏ ራዕይ ያለው ወጣት መንገዱን ያስተካክላል፤ መንገዱን ካስተካከለ ደግሞ በየት በኩል መሄድ እንዳለበት ያውቃል ብላለች። በየት መንገድ መሄድ እንዳለበት ያወቀ ወጣት አስተዋይ እንደሚሆንና ለአገሩ ምን ማበርከት እንዳለበት በደምብ እንደሚረዳ ገልጻ ለወጣቶች የሚሰጠውም ስልጠና ይህን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ተናግራለች። ድርጅቱ በዋንኛነት ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዓመት ለሁለት ሺህ ወጣቶች የህይወት ክህሎት ስልጠና የመስጠት ዕቅድ እንዳለውም አስታውቃለች። የኢምፓወሪንግ ኔክስት ጄኔሬሽን ኢትዮጵያ ምስረታ ላይ የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወጣት አልዓዛር ዘላለም 'ያለምሸት' የሚል ርዕስ ያሳተመውን ባለ 117 ገጽ የግጥም መድብል መጽሐፍና ሲዲ አስመርቋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የመረቁት የግጥም መድብል ሽያጭ ገቢ ሙሉ ለመሉ ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት ይውላል። በወቅቱ በሁለት ሰዓሊያን የተሰራና የኢትዮጵያ ቅርሶችን የሚያሳይ ስዕልም ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተበረከተ ሲሆን ዶክተር ሂሩት ተረክበዋል።