ቀጥታ፡

ቅርሶችን ከአደጋ ለመጠበቅ እየተሰራ ነው

ነሐሴ 25 /2011 ዓም ኢዜአ የኢትዮጵያ አንጡራ ቅርሶች የተጋረጠባቸውን አደጋ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። ትናንት ማምሻውን ‘ባህልና ዲፕሎማሲ’ በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ካደረጉ የውጭ አገራት ኤምባሲዎች ጋር የባህል ትርዒት ተደርጓል። በርካታ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ለአምባሳደሮቹ በአውደ-ርዕይ መልክ ቀርበው የአገሪቱን የቀደመ ሥልጣኔና ታሪካዊ ኩነቶች አሳይተዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ አገሪቱ የተለያዩ ቅርሶችን በዓለም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መዝገብ ላይ አስፍራለች። እነዚህም ቅርሶች የሕዝቦችን አንድነት፣ ሥልጣኔ፣ ባህልና ከዚህም ባለፈ የሕዝቦችን ማንነት፣ አንድነት፣ አብሮነትና እሴት የሚያንጸባርቁ ትልቅ መግለጫዎች ናቸው ብለዋል። በአገር ዴሞክራሲ፣ እኩልነትና ብልጽግና ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥም ቅርሶች የሕዝቦችን የአብሮነት እሴት በማጎልበት ይረዳል ነው ያሉት። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ቅርሶች ላይ የተፈጥሮ አደጋ መደቀኑን ጠቅሰው ይህንንም ለመከላከል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ለአብነትም ከኢጣልያ መንግሥት ጋር በመተባበር የአክሱም ሃውልትን እንዲሁም የፈረንሳይ መንግሥትም የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያን ለመጠገን የሚደረገውን ጥረት ለአብነት ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ የአሜሪካ ኤምባሲ ደግሞ የጅማ አባ ጅፋር ቤተ-መንግሥትን ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት አንስተዋል። በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (ዩ ኤን ዲ ፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ቱርሃን ሳለህ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠው ትኩረት አድንቀዋል። በኢትዮጵያ በዘርፉ የሚደረገውን ልማት ዩ ኤን ዲ ፒ እንደሚደግፍ ገልጸው በመጪዎቹ ዓመታት ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አመላክተዋል። በተለይም ጠንካራ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ቅንጅታዊ አሰራር ከተዘረጋ፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ከጎለበተና የልማት አካላት ድጋፍ ካደረጉ መጪው ጊዜ ብሩህ ይሆናል ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም