ቀጥታ፡

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋትና በጥራቱ ተወዳዳሪ ለማድረግ ድጋፍ ይደረጋል-የትግራይ ክልል መንግስት

መቀሌ ነሐሴ  25 / 2011 የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት በምርት ጥራት ተወዳዳሪ ለማድረግ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ፡፡ በጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት ስራና በመካከለኛና በታችኛው አመራር ደረጃ የሰለጠኑ 200 ወጣቶች በመቀሌ ትናንት ተመርቀዋል፡፡ የክልሉ የንግድና ኢንዱስቱሪ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት  የክልሉ መንግስት በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ይደግፋል፡፡ የክልሉ መንግስት ድጋፉን የሚያደርገው አገሪቱ የኢንዱስትሪውን እድገት በማስቀጠል መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጎን  ለመግባት በምታደርገው ጥረት ወሳኝ በመሆኑ ነው ብለዋል። በዚህም በዘርፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለማቃለልና አቅሙን ለማሳደግ እገዛ እንደሚያደርግም ኃላፊው አረጋግጠዋል። በክልሉ ላሉት የጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት ፋብሪካዎች መካከለኛ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች እውቀት ለማሳደግና ሽግግር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመቐለ ዩኒቨርስቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ ኃላፊ ዶክተር ክንፈ ፀጋይ ናቸው፡፡ ይህም በምርት ጥራት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ በማሽነሪዎች አያያዝና ጥንቃቄ ጉድለትና አስተዳደር ስራዎች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው በጀርመን ተራድኦ ድርጅት /ጂአይ ዜድ/ አስተባባሪነት ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ፤ ከዱላል ብራዘርስ ሊሚትድና ኤች ኤም ጋር በመተባበር መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ተወካይ ሚስኤል ሳቬታኮስቶቫ በበኩላቸው ስልጠናው የጀርመን መንግስት በመደበው ሁለት ሚሊዮን ዩሮ  እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2021   እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ የዲ ቢ ኤል ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተወካይ አቶ ልበሎ ገብረስላሴ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ በጥራትና በምርታማነት ተወዳዳሪ እንዲሆን በመካከለኛና ታችኛው አመራር ላይ ስልጠናው መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ ስልጠናው ስራዋን በጥራትና በርትታ ለመስራት የሚያስችላትን ዕውቀት እንዳገኘችበት የተናገረችው ደግሞ በስፌት ሙያ የስለጠነችው ወጣት አስቴር መዝገቡ ናት፡፡ በጥራት ተቆጣጣሪነት ሙያ የሰለጠነው አባዲ በርሀ በበኩሉ ፋብሪካው ተወዳዳሪና አትራፊ ሆኖ እንዲቀጥል ስልጠናው እንደረዳው ገልጾ፣ለቀጣይ የድርጅቱ እድገት እንዳስብ አድርጎኛል ብሏል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም