ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት አዲስ የፀደቀው የምርጫ አዋጅን አንዳንድ አንቀፆችን ተቃወሙ

ነሐሴ 24/2011 አዲሱ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ሀሳብ ሳያገናዝብ የጸደቀ በመሆኑ እንደሚቃወሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለፁ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ያካሄደው ሦስተኛው አስቸኳይ ስብሰባ  ''የኢትዮጵያ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ- ምግባር አዋጅ ቁጥር 1262/2011 በሙሉ ድምፅ  ማጽደቁ  ይታወሳል። አዋጁ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምስረታ አንስቶ እስከ መስራች አባላት ቁጥር ድረስ አዳዲስ አሰራሮችን አካቷል። አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት 10 ሺህ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመስረት ደግሞ 4 ሺህ የአባላትድጋፍ እንደሚያስፈልግ በአዋጁ የተደነገገ አንቀፅ ነው። የመንግሥት ሰራተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ በምርጫ ቅስቀሳና በውድድር የሚሳተፍ ከሆነ ያለ ደመወዝ ፈቃድ ማግኘት ይችላል የሚለው ደግሞ ሌላው ድንጋጌ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት አዋጁ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠቡና የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የሚገድቡ ናቸው ያሏቸውን  አንቀፆች አንስተው ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው ጥሪ መሰረት በአዋጁ ላይ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሃሳብ እንዲሰጡ መደረጉን ጠቅሰው የተሰጡት ሀሳቦች ሳይካተቱ አዋጁ እንዲጸድቅ ተደርጓል ብለዋል። የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት አዋጁ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በምርጫ በሚወዳደርበት ወቅት ከስራው እንዲገለል የሚያስገድድ በመሆኑ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል። በአዋጁ ለክልል ፓርቲዎች 4 ሺህ፤ ለአገር አቀፍ ፓርቲዎች ደግሞ 10 ሺህ የአባላት ፊርማ ማሰባሰብን የሚጠይቀው አንቀጽ የፓርቲዎችን አባላት ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ከመሆኑም በላይ የተዓማኒነት ችግር አለበትም ነው የሚሉት። በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን ሁሳ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በለውጥ ምዕራፍ ላይ የምትገኝ በመሆኑ ለውጡን ለማስቀጠል ጠንካራ መንግስትና  የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት የነበረው የምርጫ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች አካታችነት የጎደለው ስለሆነ በአዲስ አዋጅ እንዲቀየር መደረጉን የጠቀሱት የቢሮው ኃላፊ  በምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት በገለልተኛ አካል አዋጁ እንዲረቀቅ ተደርጓል ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዋጁን በአጠቃላይ መቃወም ሳይሆን 'በአዋጁ አሳታፊ አያደርግም' የሚሏቸውን አንቀፆች ለይተው ለሚመለተከው አካል ሊያቀርቡ እንደሚገባ አስረድተዋል። የመንግስት ሰራተኞች በምርጫ በወቅት ቋሚ ስራቸውን ለቀው እንዲወዳደሩ የሚያስገድደው የአዋጁ አንቀጽ የመንግስት እና የፓርቲ ስራ እንዲሁም ሀብት እንዳይደበላለቅ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነም ነው አቶ ሀሰን የሚናገሩት። ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ  በበኩላቸው የኢትዮጵያ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-  ምግባር አዋጅ እየተዘጋጀ በነበረበት ሂደት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላትን ያሳተፉ በርካታ ውይይቶች መካሄዳቸውን አመልክተዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ የህዝብ መድረክ በመጥራት ተመሳሳይ ውይይት ማድረጉንም አስታውሰዋል። ከእነዚህ የውይይት መድረኮች ለአዋጁ መጎልበት የሚጠቅሙ በርካታ ግብኣቶች መገኘታቸውንና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታና ዓለም አቀፉን መስፈርት መሰረት በማድረግ ይጠቅማሉ የተባሉ ነጥቦች በአዋጁ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም