ቀጥታ፡

በመጭው ጳጉሜ 1 ቀን አገራዊ የፀሎትና ምህላ ቀን እንዲሆን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አወጀ

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 24/2011 በመላው ኢትዮጵያ በመጭው ጳጉሜ 1 ቀን 2011 ዓ.ም አገራዊ የፀሎትና ምህላ ቀን እንዲሆን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አወጀ። ጉባኤው ከኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ጋር በመሆን ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው የፀሎት ምህላ አዋጅ የጉባኤው የበላይ ጠባቂዎች በተገኙበት ተነቧል። ጉባኤው አዲሱን ዓመት በአዲስ አስተሳስብ፣ ልብና አዕምሮ በመቀበል የተከሰቱ አገራዊ ግጭቶች ተቀርፈው ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ እንዲሰፍን፤ አዲሱ ዘመን ለአገርና ለወገን የተሻለ ዓመት እንዲሆን ፀሎትና ምህላ ማዋጅ አስፈልጓል ብሏል። ኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴት የገነቡ፣ የአብሮነት ታሪካቸውም በጽኑ መሰረት ላይ የታነፀ በመሆኑ በጎሳ፣ ብሄር፣ ሃይማኖት፣ ልዩነት ቢኖርም ልዩነቶቻቸውን በማስተሳሰር በአንድነት የባሕልና ሃይማኖት ፀጋቸውን አስከብረው መኖራቸውን አስታውሷል። ይህ አኩሪ ታሪክና የጋራ እሴቶች በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅ የገለጸው ጉባኤው፣ ባለንበት ዘመን በእምነት፣ በአመለካከት፣ በባህልና ልዩ ልዩ ፍላጎቶች አልፎ አልፎ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑን ገልጿል። የሃሳብ ልዩነቶች ግጭትን መፍጠራቸው የሚጠበቅና ተፈጥሯዊ ቢሆንም በተወሳሰበ መልኩ ተከስቶ በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ማስከተሉ እንዳሳሰበው ጉባኤው አመልክቷል። በኢትዮጵያ የተከሰተው ውጥረት፣ አለመረጋጋትና ግጭት እንዲወገድ፣ ይቅርታ፣ ዕርቅና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጉባኤው ሃይማኖታዊ፣ ሞራላዊ፣ ዜግነታዊ ግዴታውን ከዘወትር ጸሎት በተጓዳኝ ሲመክርና ሲገስጽ መቆየቱን አስታውሷል። የሰው ልጅ ክብር እንዲጠበቅ፣ ሰብዓዊ ርህራሄ እንዲኖር፣ ፍትህና አኩልነት እንዲሰፍን ከሁሉምና ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አንስቷል። 'ኢትዮጵያ የሁላችንም የማንነት የጋራ መገለጫ በመሆኗ ሰላምና አንድነቷ እንዲጠበቅ መክረናል' ያለው ጉባኤው፤ መጥፎ ጠባሳ እየጣለ የመጣውን ግጭት ከሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የሚቃረን በመሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል ብሏል። ስለሆነም ሁሉም ወገን የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በመገንዘብ ለይቅርታ፣ ዕርቅና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በፍጹም ቅንነት መስራት ይጠበቅበታል ነው ያለው። በሃይማኖታዊም ሆነ ማህበራዊ እሴቶች ሰው ማክበር፣ ትህትና፣ ሰላማዊነት፣ አለመግባባትን በይቅርታና በዕርቅ መፍታት የኖርነው የዳበረ ልምዳችን ነው ብሏል። ያም ሆኖ "ፈጣሪ ሁሉንም የሰው ልጅ እኩል መፍጠሩን እያወቅን፣ በተለያየ አመለካከትና ስሜት በመመራት ከእኛነት ወደ እኔነት፣ ወዳልተፈለገ ፉክክር፣ በሃይማኖት በሚወገዝ ግለኝነትና ግብዝነት ጎልቶ አየታዬ ነው" ሲልም አመልክቷል። ያለንበት ጊዜ ሁሉም አማኝ ፈጣሪውን በመፍራት ለአገርና ወገን ሰላምና ደህነንት ሲባል ለዕርቅና  ይቅርታ ዝግጁ መሆንና የህይወቱ መመሪያ ማድረግ እንደሚገባውም ገልጿል። በዚህም አዲሱን ዓመት ስንቀበል የከረመውን የተዛባ አመለካከት፣ ቂም በቀል ስሜት በማስወገድ፣ ወደፈጣሪ ንስሃ መቀበል እንደሚገባ አሳስቧል። በዚህም በመጭው ጳጉሜ አንድ ቀን 2011 ዓ.ም ለአገር  ሰላም ሃይማኖታዊ ስረዓት በሚፈቅደው መልኩ አገር አቀፍ የጸሎትና ምህላ ቀን እንዲታሰው ማወጁን ገልፅዋል። ለጸሎትና ምህላ አዋጁ  የፌዴራልና ክልል መንግስታት ባለስልጣናት፣ የጸጥታ አካላት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ እናቶች፣ ወጣቶችና የሃይማኖት አባቶች የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም