አዲሱ የሀዋሳ ምክትል ከንቲባ ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንደሚወጡ ገለጹ

90
ሀዋሳ ኢዜአ ነሐሴ 24/2011 ኃላፊነታቸውን በታማኝነተና በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አዲሱ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ገለጹ፡፡ የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ሁለተኛ ዙር ስድስተኛ ዓመት መደበኛ ጉባኤው ነው የምክትል ከንቲባውን ሹመት ያፀደቀው ፡፡ በሹመቱ መሰረት አቶ ጥራቱ በየነ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ አቶ ጥራቱ በምክር ቤቱ አባላት ፊት ቃለ መሀላ በመፈጸም ከቀድሞው የከተማዋ ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሾዳ ጋር የሥልጣን ርክክብ ካደረጉ በኋላ ባደረጉት ንግግር “የተጣለብኝን ኃላፊነት በታማኝነትና በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” ብለዋል ፡፡ ሀዋሳ ከተማ የቀድሞ ስሟን በሚያስጠብቅ ሁኔታ ሁሉም ዜጎች በሰላም የሚኖሩባትና ሀብት የሚፈሩባት እንድትሆን ከሁሉም የከተማው አመራር አካላት ጋር በመተባበርና በመደማመጥ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ አቶ ጥራቱን ለምክር ቤቱ በዕጩነት ያቀረቡት ደኢህዴንን ወክለው የተገኙት አቶ አብርሀም ማርሻሎ ተሿሚው በሲዳማ ዞንና በደቡብ ክልል በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ማገልገላቸውን ገልፀዋል ፡፡ ደኢህዴን በቅርቡ በሀዋሳ ከተማና ሲዳማ ዞን ተከስቶ በነበረው ሁከት ምክንያት የከተማ አስተዳደሩንና የዞኑን የፊት አመራሮች ከሥልጣን ማስወገዱ ይታወሳል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም