ቀጥታ፡

የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ ጽህፈት ቤት ''በገቢና የመንግሥት ንብረት ከብክነት በመከላከል እመርታ'' አስመዘገብኩ አለ

ሰመራ ነሐሴ 24 ቀን 2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  አገልግሎት የአፋር ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ''በገቢና የመንግሥት ንብረት ከብክነት በመከላከል እመርታ'' አስመዘገብኩ አለ። ጽህፈት ቤቱ 2011 በጀት ዓመትና አፈጻጸምና የ2012 ዕቅድ ዙሪያ ከሠራተኞቹ ጋር ዛሬ ተወያይቷል። የጽህፈት ቤቱ የፕላንና ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፈንታው ጀምሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ጽህፈት ቤቱ ያልተማከለ አስተዳደርን በመተግበር ገቢውን አሳድጓል። የንብረት ብክነትንም  ቀንሷል። በዚህም በኢነርጂ ሽያጭና ውዝፍ ሂሳብ 77ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ አፈጻጸሙ 92በመቶ አድርሷል። ከኢነርጂ ሽያጭ ለመሰብሰብ ከታቀደው 64ነጥብ 7ሚሊዮን ብር ማስገባቱንም አመልክተዋል። ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር  የ43ሚሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱን አቶ ፈንታው ተናግረዋል፡፡ በሪጅኑ የደንበኞች ውዝፍ ሂሳብ  በዓመት ከ100ሺህ በላይ ተሰብስቦ አያውቅም ነበር ያሉት ከፍተኛ ባለሙያው፣ከዚህ አንጻር ለመሰብሰብ 12ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ አፈፃፀሙን 90በመቶ አድርሷል ብለዋል። ግምታቸው ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ የኃይል ተሸካሚ መሥመሮችና ገመዶች እንዲሁም ተዛማጅ ንብረቶች በመሰብሰብም የንብረት አስተዳደሩን ማሻሻሉንም ተናግረዋል። በተጨማሪም  በዝቅተኛ መሥመርና ትራንስፎርመር ጥገና እንዲሁም ተበላሽተው ለረጅም ጊዜ የቆሙ  ሰባት ተሽከርካሪዎችን ጠግኖ ወደ ሥራ ማስጀመሩን አቶ ፈንታው አመልክተዋል። አዳዲስ ደንበኞችን በግብአት አቅርቦት ችግር አለመስተናገድ፣የለውጥ መሣሪያዎች አተገባበር ወጥነት መጓደል እንዲሁም ከአጎራባች ክልሎች ኃይል የሚገኙ አካባቢዎች የኃይል መቆራረጥ ችግርን በፍጥነት አልባት ያለመስጠት ችግሮች መታየታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው ተሊላ የዘርፉ አመራሮችና ሠራተኞችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና ግልጽነትና ታማኝነት የተሞላበት አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። አገልግሎቱ በአገር ደረጃ የነበረውን አደረጃጀት ባለፈው በጀት ዓመት ወዳልተማከለ አስተዳደር በመቀየር ክልል አቀፍ አደረጃጀት መፍጠሩና  ይህም አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽና ቀልጣፋ እንዳደረገው በመድረኩ ላይ ተገልጿል። አገልግሎቱ በአፋር ክልል 34ሺህ 376 ደንበኞች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም