የባለሙያዎች የክህሎት ክፍተት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ለሚታዩት ችግሮች አንዱ መንስኤ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የባለሙያዎች የክህሎት ክፍተት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ለሚታዩት ችግሮች አንዱ መንስኤ ነው ተባለ
ነሐሴ 24/2011 የፕሮጀክቶች መዘግየትንና የጥራት ጉድለትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታዩት ችግሮች አንዱ ምክንያት፤ በዘርፉ ባለሙያ ዘንድ ያለው የክህሎት ክፍተት ነው ተባለ። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከአጀት ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል። ስልጠናው የዘርፉ ተዋናዮች የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን ማቀድ፣ መተግበር፣ መከታተል፣ መቆጣጠርን ጨምሮ አጠቃላይ የግንባታ ሥራ አፈጻጸም ላይ የሚታዩ የቴክኒክ ክህሎትን ለማሻሻል የሚያግዝ ነው ተብሏል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምንድህስና ትምህርት መምህር ኢንጅነር ክብሮም ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በኢትዮጵያ የግንባታ ፕሮጀክት ማቀድን ጨምሮ እስከማብቂያው ድረስ ያለውን ሥራ ሂደት በወጉ የመምራት አቅም ማነስ በስፋት ይታያል። በዚህም የተነሳ የግንባታ ፕሮጀክቶች ይዘገያሉ፤ይህም ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው በላይ ከፍተኛ ለሆነ ተጨማሪ ወጪ ይዳርጋሉ። በመሆኑም ይላሉ ኢንጂኒየር ክብሮም የግንባታው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በግንባታ እቅድ፣ አተገባበር፣ ቁጥጥርና ክትትል ጥራት ላይ የጠራ ግንዛቤ መያዝ ይኖርባቸዋል። አያይዘውም የዘርፉ ተዋናይ ተቋማት መናበብ የሚያስችላቸውን የመረጃ ስርዓት መፍጠር እንዳለባቸው ጠቅሰው ይህም በአሁኑ ወቀት የሚስተዋለውንና አንዱ የግንባታ መሠረተ ልማት ስራ በሌላው የሚፈርስበትን አገራዊ ችግር ለመከላከል ይረዳል ብለዋል። በስልጠናው ላይ የተሳተፉት ባለሙያዎችም በውሃ ስራዎች፣ በመንገድ መሠረተ- ልማት፣ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና በቤቶች ግንባታ ላይ የተሰማሩ ተቋማት እርስ በርስ አለመናበብ በዘርፉ የተጋረጠ ችግር መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎቹ ይህንን የቆየ ችግር ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። ከእንግሊዝ አገር በመጡ ባለሙያዎች ለመጪዎቹ ሁለት ቀናት የሚሰጠው ስልጠና የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን የመምራቅ አቅምን ከማሳደግ ባሻገር ለዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣትም የራሱን ሚና እንደሚጫወት ነው የስልጠናው አዘጋጆች የሚናገሩት።