"የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ' በፎቶ ግራፊ ሙያ ለዓለም ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ የእውቁ ኬንያዊ ፎቶ ጋዜጠኛ መሐመድ አሚን ልጅ ሳሊም አሚን ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
"የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ' በፎቶ ግራፊ ሙያ ለዓለም ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ የእውቁ ኬንያዊ ፎቶ ጋዜጠኛ መሐመድ አሚን ልጅ ሳሊም አሚን ገለፁ
ነሐሴ 24/2011 "የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ' በፎቶግራፊ ሙያ ለዓለም ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ የእውቁ ኬንያዊ ፎቶ ጋዜጠኛ መሐመድ አሚን ልጅ ሳሊም አሚን ገለፁ። ሳሊም አሚን በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው ከሚሲዮኑ ጋር በመተባበር "የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ' በፎቶግራፊ ሙያ ለዓለም ማስተዋወቅ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ከአምባሳደር መለስ ዓለም ጋር መክረዋል። ታዋቂው የፎቶ ጋዜጠኛ መሐመድ አሚን በኢትዮጵያ ድርቅ ተከስቶ በነበረበት በ1977 ዓም ባነሷቸው እና ለዓለም ዕይታ ባበቋቸው ፎቶግራፎች ይታወቃሉ። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ኢትዮጵያ እንደ ማናቸውም የዓለም ሀገራት በታሪኳ የተፈጠሩ ክስተቶች "አሉታዊ ጎኖችም" ያሉት መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ግን የሚጠቅመው በአሉታዊ ገጽታው ላይ ማተኮር ሳይሆን ሀገሪቱ ለዓለም ስልጣኔ ባበረከተቻቸው በጎ አስተዋፅኦዎች ላይ መሆን አለበት ብለዋል። ኢትዮጵያ ለዓለም ታሪክ መዛግብት ያስመዘገበቻቸውን ዘመን ተሻጋሪ በጎ አሻራዎች ማስተዋወቅ አፅንኦት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው አምባሳደር መለስ የተናገሩት። ሳሊም አሚን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው በሙያቸው የሀገሪቱን በጎ ገፅታ ለመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከሚሲዮኑ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ተናገረዋል። የኢትዮጵያውያን ጥልቅ የሀገር ፍቅር ልዩ መሆኑን ገልፀው "ኢትዮጵያውያን አንድ ስትሆኑ የገናና ታሪክ ባለቤት ናችሁ" ብለዋል። ከዚህ ቀደም “Kenya: Through My Father’s Eyes” በተሰኘ መጽሐፋቸው የኬንያን ታሪክ እና በጎ ገፅታ የሚያሰተዋውቅ ፈጠራ የታከለበት መፅሐፍ ያሳተሙት ሳሊም አሚን በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ስራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ግልፀዋል። መሐመድ አሚን በ1983 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በመስክ ስራ እያሉ በተፈጠረው የጎተራው ፍንዳታ አደጋ የግራ እጃቸውን አጥተው ነበር። ሕይወታቸው ያለፈው ህዳር፣ 1988 ዓ.ም. በኮሞሮስ ደሴት በአጋቾች ጥቃት በተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 961 መሆኑይታወሳል። በሙያቸውም ኢትዮጵያን በተመለከተውና “Journey Through Ethiopia” በተሰኘው ሥራቸው በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ።