የኢትዮ-ጃፓን ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ጃፓን ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሄደ
ነሐሴ 24/2011 ሁለተኛው የኢትዮ-ጃፓን ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም እንዲሁም ኤግዝቢሽን በጃፓን ዮካሃማ ተካሄዷል። የኢትዮ-ጃፓን ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም የተካሄደው በአፍሪካ ልማት ዙሪያ በዮኮሃማ ምክክር የሚያደርገው 7ኛው የቶኪዮ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ቲካድ ስብሰባ ጎን ለጎን ነው። በዚሁ ፎረም 180 የጃፓን ባለሃብቶች እንዲሁም 43 የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን እንዲሁም የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ) ፕሬዚዳንት ኖቡሂኮ ሳሳኪ በፎረሙ ላይ ንግግር አድርገዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ ኢትዮጵያጵያ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የጃፓን ባለሃብቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናን አስረድተዋለ። አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃንም የጃፓን ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከተለያዩ የጃፓን ኩባንያዎችና ተቋማት ለሚደረግላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ኤምባሲው ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ ያለውን አመቺ የንግድና ኢንቨስትመንት እድሎች እንዲጠቀሙ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳይሱኬ ማትሱናጋ ለተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አመቺነት አስመልክቶ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ) ፕሬዚዳንት ኖቡሂኮ ሳሳኪ በኢትዮጵያ የተሻሻለ የንግድና ኢንቬስትመንት ዕድሎች እንዳሉ እንደሚያውቁና ይህንንም በየጊዜው ለአባላቶቻቸው እንደሚያስተዋውቁ ገልጸዋል። በመድረኩ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጮች አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኢንቨሽትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በጃፓን ዮካሃማ ከተማ በአፍሪካ ልማት ዙሪያ ምክክር የሚያደርገው 7ኛው የቶኪዮ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ቲካድ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል። ከጃፓን በተጨማሪ በጥምር አዘጋጅነት የአለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽኖች ተሳትፈዋል። በአፍሪካ ልማት ዙሪያ ምክክር የሚያደርገው የቶኪዮ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ( TICAD) እ.ኤ.አ ከ1993 ጀምሮ አፍሪካ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ በጃፓን ጠንሳሽነትና አመራር ለአፍሪካ ልማት የሚካሄድ ነው።