ቀጥታ፡

ኢትዮ-ቴሌኮም ገቢውን 45 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 24/2011 ኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማጠናከርና ተወዳዳሪነቱን አስተማማኝ ለማድረግ ያስችለኛል ያለውን የሶስት ዓመት አዲስ ስትራቴጂ ዛሬ ይፋ አደረገ። በመጪው ዓመት አጠቃላይ ገቢውን 45 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማድረስ የሚሰራ መሆኑንም የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታውቀዋል። ከመጪው አዲስ ዓመት ጀምሮ ለሶስት ዓመታት የሚተገበረውን ስትራቴጂ በተመለከተ የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ መግለጫ ሰጥተዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በዚሁ መግለጫቸው "ብሪጅ" በሚል ስያሜ ስትራቴጂው የተቀረፀው ተቋሙን ብቁ፣ ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ  በማለም ነው። የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ፣ የአገልግሎት፣ የቴክኖሎጂና ኦፕሬሽን ልህቀትን መፍጠር፣ እንዲሁም የሰው ኃይል ልማት ተኮር ተቋም መገንባትና ምርጥ የሆኑ ሁለንተናዊ ተሞክሮዎችን መጠቀም የስትራቴጂው የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አመልክተዋል። ስትራቴጂው ተግባራዊ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለማርካት፣ የቴሌኮም ስርጸትን በማሳደግ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመደገፍና አጠቃላይ የአገሪቱን  ምርታማነት ለማጠናከር ይረዳል ሲሉም ገልፀዋል። ከኢንዱስትሪው ባህሪ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ፈታኝ ሁኔታዎችን በበቂ ዝግጀትና በጥንቃቄ ለመምራት የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ሃይል መገንባት የስትራቴጂው ዋነኛ ትኩረት መሆኑንም አንስተዋል። ኢትዮ-ቴሌኮም በመጪው ዓመት የዳታ ትራፊክ እድገትን መሰረት ያደረገ የፎርጂ ኔትወርክ ማስፋፊያ በአዲስ አበባና በክልል ዋና ዋና ከተሞች ተግባራዊ እንደሚያደርግም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በዚሁ መግለጫቸው አስታውቀዋል። የአለም አቀፍ ጌትወይን በእጥፍ ለማሳደግ እሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። ኢትዮ-ቴሌኮም በመጪው ዓመት የደንበኞችን ብዛት በ16 በመቶ በማሳደግ የተጠቃሚውን ቁጥር ወደ 50 ሚሊዮን ለማሳደግና አጠቃላይ ገቢውንም 45 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም