በአፍሪካ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ሜዳሊያ ብዛት 22 ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ሜዳሊያ ብዛት 22 ደረሰ
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 24/2011 በሞሮኮ እየተካሄደ በሚገኘው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት 22 ደርሷል። የአፍሪካ ጨዋታዎች ከነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ከ54 አፍሪካ አገራት የተወጣጡ 6 ሺህ ስፖርተኞች በ26 የስፖርት አይነቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በውድድር ተሳትፎ ታሪኳ ከፍተኛ የሆነው 188 ስፖርተኞችን በ13 የስፖርት አይነቶች እያሳተፈች መሆኑም ይታወቃል። ወርልድ ቴኳንዶ፣ አትሌቲክስ፣ ካራቴ፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ጅምናስቲክ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ባድሜንተን፣ ክብደት ማንሳት፣ ቼዝና ቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያ እየተሳተፈች የምትገኝባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። ካራቴ ቅርጫት ኳስ እና ቼዝ በሞሮኮው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው አዲስ የተጨመሩ የስፖርት አይነቶች እንደሆኑም የሚታወቅ ነው። ዛሬ በግማሽ ማራቶን ሴቶች ኢትዮጵያኑ አትሌቶች ያለምዘር የኋላ፣ደጊቱ አዝመራውና መሰረት በለጠ ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት የበላይነቱን መያዛቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ትናንት በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ፀሐይ ገመቹ፣ዘይነባ ይመርና ደራ ዲዳ ከአንድ እስከ ሶስት በመግባት አኩሪ ውጤት ማስመዝገባቸው የሚታወስ ነው። ውጤቱንም ተከትሎ በ6 ወርቅ በ5 ብር 11 ነሐስ በድምሩ 22 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ከተገኙት ሜዳሊያዎች አምስት ወርቅ ፣ 5 ብር ፣7 ነሐስ በድምሩ 17 ሜዳሊያዎች የተገኙት በአትሌቲክስ ሲሆን አንድ ወርቅና ሶስት ነሐስ በወርልድ ቴኳንዶ አንድ ነሐስ ደግሞ በብስክሌት ነው። በውድድሩ እስካሁን ግብጽ በ78 ወርቅ፣ በ87 ብር ፣63 ነሐስ በድምሩ 228 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የበላይነቱን የያዘች ሲሆን ናይጄሪያ በ40 ወርቅ፣ በ28 ብርና በ35 ነሐስ በድምሩ 103 ሜዳሊያ ተከታዩን ደረጃ ይዛለች። ደቡብ አፍሪካ በ32 ወርቅ፣ በ24 ብር ና21 ነሐስ በድምሩ 77 ሜዳሊያ በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን አዘጋጇ አገር ሞሮኮ በ27 ወርቅ፣ በ26 ብርና በ40 ነሐስ በድምሩ በ93 ሜዳሊያ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ከነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ነገ ፍጻሜውን ያገኛል። የአፍሪካ ጨዋታዎች ውድድር እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር እንደ ማጣሪያ ያገለግላል።