ቀጥታ፡

የኮፓ ኮካ ኮላ ብሄራዊ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ተጀመረ

ነሐሴ 24/2011 አምስተኛው የኮፓ ኮካ ኮላ ብሄራዊ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ጨዋታ ባቱ ከተማ ተጀምሯል። ውድድሩ ኮካ ኮላ ኩባንያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ብቁ የእግር ተጫዋቾችን ለማፍራት አላማውን አድርጎ የሚዘጋጅ ነዉ። ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ በመቱ ከተማ በሚካሄደዉ ውድድር ትምህርት ሚኒስቴር፣ ኮካኮላ ኩባንያ፡ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፤የስፖርት ኮሚሽን እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል። የኮካ ኮላ ፍራቻይዝ ስራ አስኪያጅ አቶ አለም አለማየሁ በውድድሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እስካሁን 2 ሺህ 500 ኪሎ ግራም በላይ አሮጌ የፕላስቲክ ጠርሙሶችና ኮርኪዎች በአዲስ አበባና በድሬድዋ ከሚገኙ 13 ትምህርት ቤቶች ተሰብስቧል። በዚህም አሸናፊ ለሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የእግር ኳስ ሜዳ ግንባታ ማካሄድን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ መሳሪያዎች ይበረከትላቸዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ባለሙያ አቶ መኮንን ኩሩ እንደሚሉትም ላለፉት ሶስት ወራት ሲካሄድ በነበረው የክልል ትምህርት ቤቶች የእግር ኳስ  ውድድር ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተጫዋቶች ማግኘት ተችሏል። ፌዴሬሽኑ በቀጣይም ወጣቶች ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና የተሻሉ ስፖርተኞች እንዲሆኑ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። የኮፓ ኮካ ኮላ አመታዊ ውድድር እድሜያቸዉ ከ15 አመት በታች የሆኑ ታዳጊ ወጣቶችን በማሳተፍ አቅማቸውን ማጎልበት እንዲችሉ አላማው ያደረገ ነው። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ከ8 ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳደሮች የተወጣጡ ከ45 ሺህ በላይ ታዳጊዎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም