ቀጥታ፡

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ970 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ነሀሴ 24/2011 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ970 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ ገንዘቡ የተሰበሰበው ከህዝብ ድጋፍ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡ ፅህፈት ቤቱ ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ መረጃዎችን በስፋት ለህብረተሰቡ በማድረስና በቦንድ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እየሰራሁ ነውም ብሏል፡፡ ከሚመለከታቸው የገንዘብ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በቦንድ አሻሻጥና አመላለስ ዙሪያ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ላይ እንደሚገኝም ነው ፅህፈት ቤቱ የገለፀው፡፡ በ2011 በጀት ዓመት ሁለት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎች ግድቡን መጎብኘታቸውንና  የተለያዩ ተቋማትም የጉብኝት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ፅህፈት ቤቱ በቀጣይ በጀት ዓመትም ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ለማከናወን ማቀዱን ነው ያስታወቀው፡፡ ዕቅዱም በሚመለከታቸው አካላት ውይይት ተደርጎበት በሥራ አስፈፃሚ መፅደቁንና የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል፡፡ ነዋሪዎች፣ መገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ ተቋማት በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸውና በሞራል ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን በአዲሱ ዓመት የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሲልም ጽህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም