የሐይማኖት መሪዎች ስለሰላምና አብሮነት የሚሰጡት አስተምህሮ ማጠናከር አለባቸው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የሐይማኖት መሪዎች ስለሰላምና አብሮነት የሚሰጡት አስተምህሮ ማጠናከር አለባቸው ተባለ
ሀዋሳ ኢዜአ ነሀሴ 23/2011 የሐይማኖት መሪዎች የሰው ልጆች እኩልነት ፣ የሠላምና የአብሮነት አስተምህሮዎችን ለምዕመናን በማሳወቅ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ ፡፡ የኢትዮጵ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሲዳማ ዞንና ሀዋሳ ከተማ ከሚገኙ የሐይማኖት መሪዎች ጋር በግጭት አፈታትና የሠላም ግንባታ ዙሪያ ለሁለት ቀናት በሀዋሳ ከተማ ምክክር አድርጓል ። የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ጉባኤው በሀገሪቱ ለዘመናት የዘለቀውን ሐይማኖታዊ አስተምህሮዎች ላይ የተመሰረተ የሠላምና አብሮነት እሴት በመገንባት ኢትዮጵዊ አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር ሁሉን አቀፍ ጥረት በማድረግ ላይ ነው ፡፡ እስከ አሁን ድረስ የተገኘው ውጤት አበረታች ቢሆንም ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ከዚህ በላቀ ደረጃ መስራት የሚጠይቅ እንደሆነም አስረድተዋል ፡፡ የሰው ልጆች እኩልነትና ክብር ፣ ሠላም ፣ አብሮነትና ዕርቅ የሁሉም ሐይማኖቶች የጋራ አስተምህሮዎች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ፀሐፊው የሐይማኖት መሪዎች እነዚህን አስተምህሮዎች የማሳወቅ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል ፡፡ በሐይማኖቶች ውስጥ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሠጣቸው እነዚህ የሠላም እሴቶች ምዕመናንም አክብረው መኖር እንደሚገባቸው ነው ያስገነዘቡት ፡፡ ኢትዮጵያ አንድነቷን አስከብራና ሉአላዊነቷንም አስጠብቃ ለዘመናት የኖረችው ልዩነቶቻቸውን በፀጋ ተቀብለው የሚኖሩና በሀገር ጉዳይ ላይ ያለ ምንም ልዩነት በጋራ የሚቆሙ ህዝቦች ባለቤት በመሆኗ ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እያገጠሙ ያሉ ጫፍ የወጡ ብሔር ተኮር የሚመስሉ ግጭቶች ከታሪካችንና ማንነታችን ጋር አብረው የማይሄዱ አሳፋሪ ተግባራት በመሆናቸው ልንጠየፋቸውና በተግባር ልናወግዛቸው ይገባናል ብለዋል ፡፡ የሲዳማ ህዝብም ሆነ ሌሎች የተለያየ ማንነት ያላቸው ህዝቦች የሚያቀርቡትን የመብት ጥያቄ የኢትዮጵያ ሐይምኖት ተቋማት ጉባኤ እንደሚያከብር ገልፀው ነገር ግን የሚቀርብበት አግባብ ፍፁም ሠላማዊ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል ፡፡ በዞኑ በተከሰተው አለመረጋጋት የሕይወት መጥፋት ፤ ሥነ-ልቦናዊና አካላዊ ጉዳት እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ የሚያሳዝን ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ያለመግባባቱ መንስኤ ሌላ ሆኖ ሳለ ከብሔርና ማንነት ጋር ከመገናኘቱም አልፎ ሐይማኖትን በሽፋንነት መጠቀም ሊወገዝ የሚገባው ተግባር እንደሆነ አመልክተዋል ፡፡ ይህንን የፈተና ወቅት ለማለፍ ቅድሚያ ለሀገርና ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ ክብር በመስጠት በአንድነት መቆም እንደሚገባም ጠቁመዋል ፡፡ በደቡብ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የሐይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ፎከራ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተከሰቱ ያሉትን አለመግባባቶችና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረወል ፡፡ አሁን ላይ እየታየ ላለው አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋትም ጉባኤው ያበረከተው አስተዋፅኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ ነው የተናገሩት ፡፡ ክልሉ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያና የተለያዩ ሐይማኖቶች ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው መላው የክልሉ ህዝብ ልዩነቶችን እንደመልካም ፀጋ በመቁጠር ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ መኖሩን አውስተዋል ፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ጥቂት ግለሰቦች የህዝቡን አብሮነትና ሠላም ለማናጋትና እርስ በእርስ ለማጣላት እየተሯሯጡ እንደሚገኙ ፤ ይህም የከሰሩ ፖለቲከኞች ሴራ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ የተከሰተውን የዘረኝነትና ጽንፈኝነት የወንጀል ተግባር የፈፀሙና ያስፈፀሙ ግለሰቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለፍርድ እንደሚቀርቡ በክልሉ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ያለማመንታት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል ፡፡ የደቡብ ክልል እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ኡስታዝ መሀመድ ሙስጠፋ ወጣቱ ትውልድ የሐይማኖት መሪዎችንና ወላጆቹን እዳያከብርና እንዳይታዘዝ ብሎም በአንድነቱ ላይ የጸና አቋም እንዳይኖረው ምክንያት የሆነው ባለፉት አመታት በሐይማኖት ተቋማት ላይ እና በመሪዎቻቸው ላይ የነበረ የፖለቲካ ጫና እንደነበር ተናግረዋል ፡፡ እንደ ኡስታዝ መሀመድ ገለፃ የሐይማኖት ተቋማት ከመለኮታዊ ትምህርቶች ይልቅ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች የሚንሸራሸሩባቸው ወጣት ምዕመኖቻቸውን በሚገባ ሳያንፁ የሚያሳድጉ ነበሩ ፡፡ ከዚህ ችግር ለመሻገርም የሐይማኖት ተቋማት መለኮታዊ አስተምህሮቶችን ከፖለቲካ አጀንዳ ጋር ሳይቀላቅሉ ነፃ ሆነው በሠላምና በሀገራዊ አንድነት ላይ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳዎች ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ላአከ ወንጌል ቀሲስ ደግፌ ባምቡራ የሐይማኖት አባቶች ስለሰላምና ፍቅር የማስተማር ኃላፊነት ለመወጣት እየሰሩ ቢሆንም በዚህ ልክ ውጤት ሳይገኝ መቅረቱን ገልፀዋል ፡፡ ሁላችንም የሐይማኖት መሪዎች የችግሩን መንስኤ ከራሳችን ጀምረን መፈተሽ አለብን ያሉት ላአከ ወንጌል ቀሲስ ደግፌ ለመፍትሔውም በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት ፡፡ በኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የአለታ ወንዶ ወረዳ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ሕብረት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዶክተር በራሳ የሐይማኖት ተቋማት በሰላምና አንድነት ጉዳይ ላይ በጋራ መምከራቸው አሁን ላይ እየታየ ላለው ችግር መፍትሔ ለማበጀት ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል ፡፡ ከምክክር መድረኩ ያገኙትን የሀሳብ ግብዐት በመጠቀምም ወጣቶችን የሚያንጹ ተግባራት ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ነው የገለፁት ፡፡ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ከኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ እንዲሁም ከሲዳማ ዞንና ሀዋሳ ከተማ የተውጣጡ የሐይማኖት መሪዎች ተሳትፈዋል ፡፡