ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ምርምሮችንና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ ነው---የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት

አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን ለመስራትና በመስኩ ብቃት ያለው የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ዩንቨርስቲው በዛሬው እለት የምርምር ቀንን የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ይፋ በማድረግ አክብሯል። በዚህ ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንደገለጹት ተቋሙ ብቃት ያለው የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በመስራትና ለህብረተሰቡ በማሰራጨት ረገድ በትኩረት ይሰራል። በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ለአገሪቷ ልማትና እድገት በሚጠቅሙና ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር በተጣጣሙ 26 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የምርምር ስራዎቸን እየሰራ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን የመስራት፣ የምርምር ሥራዎቹ በተሰሩበት አካባቢ ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅና በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታተሙ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በተለይ የምርምር ሥራዎቹን የተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች እንዲተዋወቋቸውና ስራ ላይ እንዲያውሏቸው የማድረግ ተግባርም መሰራቱን አክለዋል። ይሁንና በፋይናንሰ ህግና እጥረት፣ እንዲሁም በአቅም ክፍተት አብዛኛዎቹ ምሁራን ከምርምር ሥራዎች ይልቅ የማማከር አገልግሎት ላይ በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። በመሆኑም በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍና የምርምር ሥራዎች በብዛትና በጥራት እንዲወጡ ለማገዝ የፋይናንስ ህግ እንዲሻሻል፣ ለምርምር የሚመደበው በጀት በእጥፍ እንዲያድግና ለተመራማሪዎች የተለያዩ ማበረታቻዎች እንዲኖሩ ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዘርይሁን ወልዱ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ የተማረ የሰው ኃይልና  የጥናትና ምርምር ስራዎች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ ይገኛሉ። የምርምር ቀኑ ሲከበር ለአገር የሚጠቅሙና ለልማት የሚውሉ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች መቅረባቸው በምርምር የተለዩትን ችግሮች እስከ መፍትሄው ለፖሊሲ አውጪዎች ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት ለተመራማሪዎች እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በመመደብ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ምርምሮችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የምርምር ቀኑ ተሳታፊች በበኩላቸው የቀኑ መከበር የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የሰሯቸውን የምርምር ስራዎች ለማወቅ፣ ለመገንዘብና ለህብረተሰቡ ለማድረስ ያስችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከተሳታፊዎቹ አንዱ ዶክተር ዳንኤል ሰይፉ እንደገለጹት የምርምር ቀኑ ሲከበር የተለያዩ የምርምር ስራዎች መቅረባቸው በአገሪቷ ያሉትን ችግሮች አውቆ በተናጥልና በቡድን ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ለመስራት ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል። በእንስሳት ላይ ጥናትና ምርምር ያቀረቡት ዶክተር ዲንቃ አያና ደግሞ በምርምር ቀን የሚቀርቡት ምርምሮች የእንስሳት ሃብትን በማጎልበት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ጠቃሚ ነው ሲሉ ገልጸዋል። የጥናት ምርምር ቀን ሲከበር በተመራማሪዎች የሚቀርቡት የጥናትና ምርምር ውጤቶች ውስን የሆነውን የአገሪቷ ሃብቶች ለማወቅና በአግባቡ ለመጠቀም ከፍተኛ እስተዋጾኦ አለው ያሉት ደግሞ ዶክተር ፈለቀ ዘውገ ናቸው። ዩኒቨርሲቲው የምርምር ቀኑን በየዓመቱ የሚያከበር ሲሆን በዛሬው እለትም 29 የሚሆኑ የምርምር ስራዎች ቀርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም