ቦርዱ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውስኔ መስጫ ቀን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ቦርዱ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውስኔ መስጫ ቀን ይፋ አደረገ
ነሐሴ 23/2011 ኢዜአ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውስኔ መስጫ ቀን ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚሆን አስታወቀ።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈጽምለት መጠየቁ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ቦርዱ አመራሮቹ ከተሟሉለት በኋላ ባደረገው ውይይት የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉንና ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤም ቦርዱን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ማድረግ የሚገባቸውን ዝግጅቶች በዝርዝር ማሳወቁን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስፍሯል።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ነሃሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ህዝበ ውሳኔው የሲዳማን ክልል መሆን ቢያረጋግጥ የሃዋሳ ከተማን አስመልክቶ ሁለቱ አካላት ስለሚኖራቸው ግንኙነትና የሃብት ክፍፍል ህግ ለማውጣትና ህጋዊ ማእቀፍ ለማዘጋጀት እንዲሁም በዞኑ የሚኖሩ የሌሎች ብሔረሰብ አባላት ስለሚኖራቸው መብትና ጥበቃ ከህገ መንግስቱ በተጨማሪ አስተዳደራዊና ህጋዊ ማእቀፎችን ለማዘጋጀት ጊዜ ስለሚያስፈልግ አሁን ማቅረብ እንደማይችል ገልጾ ነገር ግን ከህዝበ ውሳኔው አስቀድሞ የህግና አስተዳደራዊ ማእቀፎቹን በማጽደቅ እንደሚያቀርብ ማረጋገጡ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ቦርዱ ከነሃሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የህዝበ ውሳኔውን የድርጊት መርሃ ግብርና በጀት አዘጋጅቶ ለደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት የላከ ሲሆን በእቅዱ መሰረት የህዝበ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ቀን ህዳር 03 ቀን 2012 ዓ.ም ይሆናል ነው የተባለው።
በድርጊት መርሃ ግብሩ መሰረት ቦርዱ የባለድርሻ አካላትን ማስተባበርና የአፈጻጸም ውይይት የማድረግ ስራውን ከነሃሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ባሉት ሳምንታት የሚያከናውን ሲሆን፤ ከዚህም ተጨማሪ የ8 ሺህ 460 ምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመል፤ 1 ሺህ 692 የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ማደራጀት፣ የህዝበ ውሳኔ መመሪያዎች የማውጣትና የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት የመሳሰሉትን ስራዎች ያከናውናል።
ቦርዱ ከመስከረም 07 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮም የህዝበ ውሳኔውን ጸጥታና ደህንነት ጥበቃ የእቅድ ዝግጅት ለማከናወን ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን የጸጥታ አካላት ጋር የጋራ እቅድ የማውጣት ውይይቶችን እንደሚያደርግ ነው በመግለጫው ያብራራው።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የሀዋሳን ከተማ የወደፊት ሁኔታ ፣የሀብት ክፍፍልና የሌሎች ብሄረሰብ አባላትን የመብት ጥበቃ አስመልክቶ ህጋዊና አስተዳደራዊ ማእቀፎችን የማውጣት ስራንም እስከ መስከረም 22 ቀን 2012ዓ.ም ድረስ የሚያጠናቅቅ ይሆናል።
ከዚህ ባለፈም የክልሉ ምክር ቤት ቦርዱ ባቀረበው ዝርዝር የበጀት እቅድ መሰረት ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን 75 ሚሊዮን 615 ሺህ 015 ብር በጀት እስከ መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ወደ ቦርዱ የባንክ አካውንት የሚያስተላልፍ ይሆናል።
ቦርዱ የቴክኒክ ጉዳዮችን በቀሪው ጊዜ ሲያጠናቅቅ ባለድርሻ አካላት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በመወጣት ሕዝበ ውሳኔው በታቀደለት ጊዜ መሰረት እንዲከናወን የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።