የመገናኛ ብዙሃኑ ችግር ከመጠን በላይ የመደመርና ከመጠን በላይ የመቀነስ አዝማሚያ ነው - ዶክተር ወዳጄነህ መሃረነ - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃኑ ችግር ከመጠን በላይ የመደመርና ከመጠን በላይ የመቀነስ አዝማሚያ ነው - ዶክተር ወዳጄነህ መሃረነ
ነሐሴ 23 / 2011 የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከዩ.ኤን.ዲ.ፒ ጋር በመተባበር ''የአገራችን ሚዲያ በሕዝብ ዕይታ" በሚል መሪ ሃሳብ ቢሾፍቱ ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ነው። የውይይት መድረኩ ተሳታፊ ዶክተር ወዳጄነህ መሀረነ ከለውጡ በኋላ የመጣውን የሃሳብ ነጻነት ተከትሎ የመገናኛ ብዙሃኑ በሁለት የተለያዩ መንገዶች እየተጓዙ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ዶክተር ወዳጄነህ የመገናኛ ብዙሃንን ነባራዊ ሁኔታ ከመጠን በላይ መደመርና ከመጠነ በላይ መቀነስ ብለውታል። ይህ ማለት መንግስትን ፍጹም የመደገፍና ፍጹም የመቃወም አዝማሚያ እንደሆነም አብራርተዋል። ሙያውን ያለ አግባብ የመጠቀም የወገንተኝነት ስሜት፣ የክህሎት ማነስ እና ሌሎች የጋዜጠኝነት መርሆዎችን የመጣስ ሁኔታ እንደሚስተዋልም አውስተዋል። መገናኛ ብዙሃን የኅብረተሰቡን ችግር ነቅሶ ያለማውጣት፣ ድክመቶችን ያለማሳየት እንዲሁም ጠንካራ ጎኖችን ያለማጉላት ችግሮች ይታዩባቸዋል ሲሉ ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎችም ተናግረዋል። የጋዜጠኛው የዝግጁነት ማነስ፣ ለሙያው ስነ-ምግባር ተገዝቶ ለህዝብ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን ለይቶ ያለማቅረብ ችግርም ተጠቅሷል። ኃላፊነትን ከመወጣት ይልቅ ገንዘብ ተኮር የመሆን አዝማሚያ መኖሩ አሉታዊ ሚና እንዳለውም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። የመገናኛ ብዙሃኑ ራሳቸውን መቃኘት፤ መንግስትና የሙያው ማህበራትም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳሚገባቸውም ሃሳብ ተሰንዝሯል። አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ የሙያውን ስነ-ምግባር አክብሮ በአገራዊ አንድነት ላይ የሚሰራ ሚዲያ የማጠናከር አስፈላጊነትም ተነስቷል።