በምርምር የተደገፈ የመንገድ ግንባታ ለጥራት፣ ዘላቂነትና ወጪ ቆጣቢነት ወሳኝ ነው - ጥናት - ኢዜአ አማርኛ
በምርምር የተደገፈ የመንገድ ግንባታ ለጥራት፣ ዘላቂነትና ወጪ ቆጣቢነት ወሳኝ ነው - ጥናት
አዲስ አበባ ነሀሴ 23/2011 በምርምር የተደገፈ የመንገድ ግንባታ ስራ ጥራቱን የጠበቀ ዘላቂና ወጪ ቆጣቢ ስራ ለመስራት እንደሚያስችል በዘርፉ የተደረገ ጥናት አመለከተ። በኢትዮጵያ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን በምርምር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የመንገድ ምርምር ማዕከል ገለጸ። ስድስተኛው የመንገድ የምርምር ጉባኤ ''ውጤታማ የመንገድ ትስስርን በምርምር ማረጋገጥ'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሔደ ይገኛል። በምርምር ጉባኤው ላይ በመንገድ ደህንነት፣ ለመንገድ ግንባታ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች እንዲሁም የመንገድ ብልሽትን መጠገን ላይ ያተኮሩ የምርምር ውጤቶች ቀርበዋል። የምርምር ስራቸውን ካቀረቡት ምሁራን መካከል አንዱ የሆኑት ኢንጅነር ዘበነ አባቡ እንደሚሉት፤ የመንገድ ዘርፍን በምርምር ማገዝ የመንገድ ግንባታ ጥራት እንዲጠበቅ በማድረግ ዘላቂና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ዘርፉን በምርምር ማገዝ የመንገድ ተደራሽትን እንደሚያሳድግም ገልጸዋል። በመንገድ ግንባ ወቅት ሴራሚክን ከአሸዋ ጋር ቀላቅሎ በግብዓትነት መጠቀም ለመንገድ ጥራት ጠቃሚ መሆኑን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። ግኝቱ አሁን በአገሪቷ በስፋት እየታየ ያለውን ከመንገድ ግንባታ በኋላ የሚያጋጥመውን የመንገድ መሰነጣጠቅ ችግር እንደሚያቃልል ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ይታገሱ ደሳለኝ በበኩላቸው የመንገድ ምርምር ማዕከሉ የዘርፉን ችግሮች በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ማዕከሉ እስካሁን ባካሄደው ጥናት በተለይ ደግሞ በመንገድ ዲዛይን ዘርፍ ጎላ ያሉ ችግሮች እየታዩ መሆኑን ጠቁመዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ማዕከሉ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ራሱን የቻለ የዲዛይን ክፍል አቋቁሞ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል። በተለይ ደግሞ ማዕከሉ በእስካሁኑ ስራው ቴክኖጂን መሰረት ያደረጉ የመንገድ ግንባታና ጥገና ዘርፍ አሰራሮችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያመለክት የምርምር ስራዎችን መስራቱን ተናግረዋል። በተጨማሪም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመሆን የመንግድ ፕሮጅክቶች ግንባታ መዘግየት ችግርን ለመፍታት የፕሮጀክት አስተዳደር ላይ ውጤታማ ስራዎች እንደተሰሩ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በማዕከሉ አማካኝነት በሚጠኑ ጥናቶች የሚሰጡ ምክረሃሳቦች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ አለመሆኑን ዳይሬክቱ አንስተዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እንጂነር ሐብታሙ ተገኝ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘርፉን በምርምር አስደግፎ እየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ ደግሞ ''ባለስልጣኑ ዘመናዊ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ ሆኖ የተሻለ የመንገድ ዲዛይን፣ ግንባታና ጥገና ዘዴን ለመጠቀም እየሰራ ይገኛል ነው'' ያሉት። ማዕከሉም ለአገሪቷ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ለምስራቅና ለመካከለኛው አፍሪካ አገሮች ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።