ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋማትና የሚሰጡት አገልግሎት ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው

ነሐሴ 23/2011 “የሀገራችን የሚዲያ ተቋማትና የሚሰጡት አገልግሎት በህዝብ እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ  ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ተሳታፊዎች በተገኙበት በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር ጌታቸው ድንቁ፤  ውይይቱ  ህዝቡ ስለሚዲያዎች አገልግሎት ያለው እይታ ምን እንደሚመስል ሃሳቦችን ለመለዋወጥና  የሚዲያዎችን ጥንካሬና ድክመት  በህዝብ ዕይታ ለመጠቆም ነው ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዜሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ ያገኙትን አንጻራዊ ነጻነት ተከትሎ የሙያ ስነምግባር ጉድለቶች እና ገለልተኛ ያለመሆን ችግር እየተስተዋለባቸው ነው ብለዋል።

የሚዲያዎችን ክፍተት ለመቅረፍና አቅማቸውን ለማሳደግ መንግስት በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በኩል እየሰራ ቢሆንም ህዝቡም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የተናገሩት።

በምክክር መድረኩም ሚዲያዎች በማስተማር፣ በማሳወቅ፣ በማዝናናት አገልግሎት እያሳዩ ያለው ጥንካሬና ድክመት ይዳሰስበታል ብለዋል።

በመድረኩ የመወያያ ሃሳብ ያቀረቡት ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ እንዳሉት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የእውቀት፣ የባህልና ቋንቋ አጠቃቀም ክፍተት አለባቸው ነው ያሉት።

ማህበረሰብን የማገልገል ግባቸውን የሚረሱ ሚዲያዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

የሀገሪቱ ጋዜጠኞች በልምድ፣ በሙያ የሚሰሩና አብዛኞቹ  ያለ ልምድ  ከውጪ የተኮረጁ ፕሮግራሞችን ብቻ የሚያቀርቡ በሚልም በሁለት ከፍለዋቸዋል።

“ፕሮግራም አዘጋጆች ከማስታወቂያ ገቢ ምን ያህል አገኛለሁ” ከማለት በህብረተሰቡ በሚያመጡት ለውጥ ራሳቸውን ሊለኩት  እንደሚገባም ነው ዶክተር በድሉ የተናገሩት።

ሌላው የመወያያ ሃሳብ ያቀረቡት ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው፤ሚዲያዎች የማህበረሰቡን ባህልና እሴት መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል ።

ሀገር እና ማህበረሰብ ሲገነባ የሚዲያው ሚና ትልቅ ነው ያሉት  ኡስታዝ አቡበከር ሙያዊ ስነምግባርን በመጠበቅ እውነትን ወደ ህዝብ የማድረስ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የሀገሪቱ ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች በፖለቲካ ለውጦች ምክንያት ተጽዕኖ ውስጥ መግባታቸው፣ ነጻ የሚዲያ ተቋማት ባለመገንባታቸው በህዝብ ዘንድ አመኔታን ማጣታቸውና ከመገናኛ ብዙሃን ይልቅ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ ሊቀረፍ ይገባል ነው ያሉት።

ሚዲያዎች ወደ አንድ የመወገን በተለይ የክልል ሚዲያዎች የሚያሳዩት ከሙያዊ ምግባር ያፈነገጡ አቀራረቦች ጎጂ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

የሚዲያ ሃላፊዎችም ገለልተኛ ሆነው የተለያዩ ሃሳቦችን በማቅረብ ህዝቡ እውነታን በራሱ ሚዛን  እንዲወስድ ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ኡስታዝ አቡበከር የመከሩት።

ሌላው የመወያያ ጽሑፍ አቅራቢ ዶክተር ወዳጄነህ መኃረነ፤ መገኛና ብዙሃን ራሳቸውን በአራት መስታወቶች ማየት አለባቸው ብለዋል። እነዚህም የጋዜጠኞች ስብዕና፣ የመረጃ ምሉዕነት፣ የሚዲያ እውነትን የመዘገብ ሙያዊ ስነምግባር ና የፕሮግራሞች ይዘት እንደሆኑ ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ ሚዲያ ከአራቱ እይታዎች አኳያ ለመንግስትና ለብሔር ፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኛ መሆን ፣ ምሉዕ መረጃ ያለማቅረብ፣ የፕሮግራሞች የይዘት ጉድለትና የጋዜጠኞች የስብዕና ጉድለት ይታይባቸዋል ብለዋል። ለቃለምልልስ የሚቀርቡ ሰዎችን የሚዘልፉ ጋዜጠኞችም አሉ ያሉት ዶክተር ወዳጄነህ፣ይህ ሊስተካከልና ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል ብለዋል። የምክክር መድረኩን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም