በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙሪያ ግንዛቤ የመስጠት ስራ ይከናወናል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙሪያ ግንዛቤ የመስጠት ስራ ይከናወናል ተባለ
ነሐሴ 22/2011 በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለማጠናከር በዴሞክራሲ መርሆዎችና በሃሳብ ነፃነት ዙሪያ ለኀብረተሰቡ ግንዛቤ የመስጠት ስራ ይከናወናል ተባለ። ''ሀሳብን በነፃነት መግለጽ የዴሞክራሲ ውጤት ነው'' በሚል መሪ ቃል ጳጉሜን 4 ቀን 2011 ዓ.ም የዴሞክራሲ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል። በዕለቱ በሸራተን አዲስ ሆቴል ''ዴሞክራሲና የሃሳብ ነፃነት'' በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ይካሄዳል። በውይይቱ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች የታቀፉ የሴቶች፣ የወጣቶችና የተማሪዎች ተወካዮችን ጨምሮ 1000 ሰዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከሰዓት በኋላ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሦስት የውይይት መድረኮች በክፍለ ከተማ ደረጃ በሦስት ቦታዎች የሚካሄዱ መሆኑን የዲሞክራሲ ተቋማቱ ተወካዮች ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ እና የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ቀኑን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል። ዶክተር ጌታቸው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የዘርፉ ተቋማት ብቻ ሳይሆን የሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ መሆን አለበት። ጳጉሜን 4 ቀን 2011 ዓ.ም በተሰየመው የዴሞክራሲ ቀን ኀብረተሰቡ ሀሳብን በነፃነት በመግለጽ በኩል ግንዛቤ እንዲኖረው የሚደረግበት መርሃ ግብር እንደሆነም አብራርተዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው "የዴሞክራሲ ቀን" ዓላማ የዴሞክራሲ መርሆዎችንና የሃሳብ ነፃነትን ለኀብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሆነም ዶክተር ጌታቸው ገልጸዋል። በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖችና የኀብረተሰብ ክፍሎች የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅስቃሴዎችን በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ማከናወን የሚያስችል አሰራርና ግንዛቤ መፍጠር ጭምር እንደሆነም አስረድተዋል። በዕለቱ የሚካሄዱ የውይይት መድረኮች በመገናኛ ብዙኃን በቀጥታ የሚሰራጩ መሆኑን ዶክተር ጌታቸው ጠቁመዋል። በተጨማሪም ባለፈው አንድ ዓመት በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን በማስወገድ ወደ ፊት ለመራመድ ትኩረት የሚደረግ ይሆናል ብለዋል። የህዝብ እንባ ጠባቂ ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በበኩላቸው የፓናል ውይይቶቹ ዜጎች አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት፣ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆኑን ገልጸዋል። የፓናል ውይይቶቹ በ10 ነጥቦች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የገለጹት ዶክተር እንዳለ የዴሞክራሲ መርሆዎችና እሴቶች፣ የዴሞክራሲ አተገባበር በኢትዮጵያ፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንጻር በለውጡ የተገኙ ውጤቶች፣ የሃሳብ ነፃነት መሰረታዊ መብቶችና ግዴታዎች የሚሉት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።