ቀጥታ፡

በሀገሪቱ ግጭቶችና አለመግባባቶችን ለመከላከልና ይቅር መባባልን ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ነሀሴ 22 ቀን 2011 በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶችን ለመከላከልና ይቅር መባባልን ለማጎልበት የሠላም ግንባታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ፡፡ የጉባኤው ከፍተኛ አመራሮች በሲዳማ ዞን አለታ ወንዶ ከተማና ሁላ ወረዳ ተከስቶ በነበረው ሁከት የተጎዱ ዜጎችን ጎብኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በጉብኝቱ ባለፈው ሐምሌ 11 ቀን 2011 በሲዳማ ዞን ተፈጥሮ በነበረው ሁከት በሰውና በንብረት እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት መመልከታቸውንና አሳዛኝ ተግባር መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡ የጥፋት ድርጊቱ የሲዳማን ህዝብ የአብሮነት እሴት እንደማይገልጽና ሊከሰት የማይገባው እንደሆነ ጠቁመው፣ የፖለቲካ ጥያቄን መነሻ በማድረግ የሃይማኖት ተቋማትን የጥቃት ሰለባ ማድረግ አግባብ እንዳልሆነም ተናግረዋል። ድርጊቱ የሃይማኖት ግጭቶች እንዲቀሰቀሱና ሀገሪቱ ወደ ቀውስ እንድታመራ ለማድረግ ታቅዶ የተሰራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት። ሁከቱ ተከስቶ በነበረበት ወቅት የሌላ ብሔር ተወላጆችን ሸሽገው ነፍሳቸውን ማትረፍ የቻሉ የሲዳማ ብሔር ተወላጆች መኖራቸውን ያስታወሱት ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ፣ “እንዲህ አይነቱ የአብሮነትና የአቃፊነት እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል ፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው በሀገሪቱ ውስጥ ግጭቶችና አለመግባባቶች እንዳይከሰቱ የሠላም ጥሪ የማስተላለፍ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል። ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላም እንዲበርዱ፣ በቀል እንዳፈጸምና ይቅር መባባል እንዲጎለብት ጉባኤው ቀጣይነት ያለው ተግባር እንደሚያከናውንም ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ተናግረዋል። "በዚህ በኩል በህዝቦች መካከል መግባባቶችን ለመፍጠር ጉባኤው የተለያዩ መድረኮችን የማመቻቸት ሥራ ያከናውናል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ፕሬዚዳንትን ወክለው በጉብኝቱ ላይ የተገኙት ሼህ ሰኢድ አህመድ “በአካባቢው የተከሰተው አሳዛኝ ድርጊት ዳግም እንዳይከሰት መሰራት አለበት” ብለዋል ፡፡ አሁን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለውን ፈተና ለማለፍ ትዕግስትና ይቅር ባይነት በእጅጉ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ሼህ ሰኢድ፣ በሕግ አግባብ የሚፈታውን ለሕግ አካላት በመተው የቀድሞውን አንድነትና መተባበር ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል ፡፡ የኢትዮጵያ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ተወካይና የጉባኤው የቦርድ አባል ፓስተር አንጋው ጌታሁን በበኩላቸው “የምንኖርባት መሬት ከፈጣሪ የተሰጠን እርስ በርስ ተደጋግፈን ለመኖርና ለማልማት እንጂ አንዳችን ሌላውን ልናፈናቅልባት አይደለም” ብለዋል ፡፡ “በቀጣይ በጥፋቱ የተጎዳውን በመካስ እንደ ቀድሞው በአብሮነት መኖር ያስፈልጋል” ሲሉም ገልጸዋል ፡፡ ተከስቶ በነበረው ሁከት ከተጎዱት መካከል የሁላ ወረዳ ነዋሪ መምህር ዮሐንስ አስፋው የሃይማኖት ጉባኤው አባላት ተጎጂዎችን ባሉበት መጥተው በማጽናናታቸው አመስግነዋል፡፡ የደረሰው ጥፋት ሁሉንም የሲዳማ ህዝብእንደማይወክልና ሁከትና ግርግር ሲነሳ ሕይወታቸውን ለማትረፍ የተሸሸጉት በሲዳማ ብሔር ተወላጆች ቤት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ “ይህ ድርጊት ዳግም እንዳይከሰት ሁሉም አጥፊዎች ለህግ መቅረብ አለባቸው” ያሉት መምህር ዮሐንስ አሁንም በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ነው የጠቆሙት ፡፡ ተጎጂዎች አስፈላጊውን ካሳ በአፋጣኝ ማግኘት እንደሚገባቸው የገለጹት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጉልላት ካሳ ናቸው ፡፡ የሃይማኖት ጉባኤው በሲዳማ ዞን ከሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በግጭት አፈታትና አስተዳደር ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በሃዋሳ ከተማ የጀመረ ሲሆን ውይይቱ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም ለማወቅ ተችሏል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም